(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 18/2010) በደቡብ ወሎ ዞን በተሁለደሬ ወረዳ የጎበያ አርሶ አደሮች በሃይቅ ከተማ ከፍተኛ ተቃውሞ ማሰማታቸው ተነገረ።
አርሶደሮቹ ተቃውሞውን ያደረጉት የእርሻ ቦታቸው፣ ለባቡር ፕሮጀክት በሚል እጅግ ዝቅተኛ በሆነ የካሳ ዋጋ የተወሰደባቸው ናቸው።
በደቡብ ወሎ የጎበያ አካባቢ በወረዳው ከፍተኛ ምርት የሚሠጥ ለም መሬትና ሀይቁን ተከትሎም ምርታማ የመስኖ ግብርና የሚከናወንበት አካባቢ ነው፡፡
በዚሁ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች ታዲያ የእርሻ ቦታቸው ለባቡር ፕሮጀክት በሚል እጅግ ዝቅተኛ በሆነ የካሳ ዋጋ ስለወሰደባቸው ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።
አርሶአደሮቹ ተቃውሞአቸውን በየደረጃው ላሉ የመንግስት አስተዳደር አካላት ቢያቀርቡም የመፍትሄ እርምጃ የሚወስድ አካል አላገኙም።
እኛ ልማቱን አንቃወምም የሚሉት አርሶአደሮቹ እጅግ ምርታማ የሆነው የመስኖ መሬት ሳይቀር በዝቅተኛ የካሳ ግምት ልቀቁ መባላችን እኛንና ቤተሠቦቻችንን በረሀብ ለመጨረስ የታለመ ነው ብለዋል፡፡
አርሶአደሮቹ የወረዳው አስተዳደር ፀጥታ ሀላፊ በጠራው ስብሰባ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር።
ይሕም ሆኖ ግን << የምንላችሁን ካልሰማችሁ በፌዴራል ፖሊስ ተገዳችሁ ትነሳላችሁ! >> በማለት እንደዛተባቸው ነው የገለጹት። ይሕም አንባገነናዊ ንግግር እጅግ አስቆጥቶናል ባይ ናቸው፡፡
ይህን ተከትሎም ከ50 በላይ የሚሆኑ አርሶደሮች በከፍተኛ ጩኸት ስብሰባውን ረግጠው በመውጣት ተቃውሟቸውን እንዳሰሙ ከስፍራው ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።
አርሶ አደሮቹ ቅሬታቸውን የሚሠማ አካል በማጣታቸው ፤ሚዳያዎች ድምፃቸውን እንዲያሠሙላቸውም ጠይቀዋል፡፡