ከ 8 ሚሊዮን ያላነሱ ኢትዮጵያዊያን አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲል ተመድ አሳሰበ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 16 ቀን 2010 ዓ/ም) በመላው ኢትዮጵያ በተከሰተ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ምክንያት ከ 8 ሚሊዮን ያላነሱ ዜጎች አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ። ከአፋጣኝ እርዳታ ፈላጊ ዜጎች ውስጥ 1.8 ሚሊዮን የሚሆኑ የርሃብ ተጠቂዎች በሶማሊያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ሕይወታቸውን ለማዳን አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ይገባቸዋል ሲል ተመድ በወርሃዊ ሪፖርቱ ገልጿል። በሶማሌ እና ኦሮሞ ብሄር ተወላጆች መሃከል ተከስቶ የነበረው የጅምላ ማፈናቀል ለርሃቡ አደጋ መባባስ ቀዳሚው ምክንያት ሆኗል።
በመላው ኢትዮጵያ በተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት አያሌ ዜጎች ከትውልድ ቀያቸው በኃይል እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል። በቅርብ ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ በተከሰተው የጅምላ ማፈናቀልና የእርስበርስ ጦርነት 1.7 ሚሊዮን ዜጎች ከትውልድ ቀያቸው ሲፈናቀሉ፣ የሶማሊያ ክልል ቀዳሚው መሆኑን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ.ኦ.ኤም አስታውቋል።
በጦርነትና በርሃብ ተጋላጭ የሆኑ ኢትዮጵያዊያንን ህይወት ለመታደግ ግብረሰናይ ድርጅቶችና መንግስት አፋጣኝ የሆነ የህይወት አድን ሥራ ሊሰሩ ይገባል ሲል ሪሊፍ ዌብ ዘግቧል።