(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 15/2010)በኢትዮጵያ እስር ቤት ለ11 አመታት ሲማቅቅ የቆየውና የካናዳ ዜግነት ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከእስር ተለቆ ወደ ቶሮንቶ መመለሱ ተነገረ።
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ በምህረት የተለቀቀው በሽር ማክትሃል የተባለው ኢትዮጵያዊ በሽብር ተከሶ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት እንደነበር ይታወሳል።
በሽር ማክትሃል ከኢትዮጵያ ወደ ካናዳ በማምራት በስደት ሲኖር ቆይቶ ዜግነት ካገኘ በኋላ ወደ ኬንያ በማምራት የልባሽ ጨርቅ ይነግድ ነበር።
ቀጥሎም በሶማሊያ ተመሳሳይ ንግድ ሲሰራ ከቆየ በኋላ እንደ አውሮፓውያኑ በ2006 በኬንያ ድንበር አቅራቢያ የኢትዮጵያ ጦር በፈጸመው ወረራ ለእስር መዳረጉን ከአምነስቲ ኢንተርናሽናልና ከካናዳ መንግስት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በዚህ ሰበብ በአሸባሪነት ተጥርጥሮ በእስር ላይ የቆየው በሽር ማክትሃል በኢትዮጵያ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ለ11 አመታት ሲማቅቅ ቆይቷል።
ከእስር እንዲለቀቅ የሕወሃትን አገዛዝ ሲወተውቱ የነበሩት አምነስቲ ኢንተርናሽናልና የካናዳ መንግስት በመጨረሻ በሽር ማክትሃል ነጻ በመውጣቱ ደስታቸውን ገልጸዋል።
በሽር ማክትሃል በእስር በቆየበት ጊዜ ከፍተኛ ሰቆቃና በደል እንደደረሰበት አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪው አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታውሷል።
ይህም ሆኖ ግን በኢትዮጵያ በተከሰተው ሕዝባዊ አመጽ ምክንያት አገዛዙ እስረኞችን ሲለቅ እርሱም ነጻ በመውጣቱ አዎንታዊ ርምጃ ነው ብሏል።
ባለፈው ቅዳሜ ካናዳ የገባው ትውልደ ኢትዮጵያዊው በሽር ማክትሃል ቶሮንቶ ሲደርስ በቤተሰቦቹና ጓደኞቹ አቀባበል ተደርጎለታል።
የበሽር ማክትሃል ቤተሰቦችም ለእርሱ መለቀቅ ምክንያት ለሆኑት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰብአዊ መብት ተከራካሪዎችና ለካናዳ መንግስት ምስጋና አቅርበዋል።