(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 11/2010) በኩባ የፊደል ካስትሮ ቤተሰብ የአገዛዝ ዘመን ሊያከትም መሆኑ ተገለጸ።
ይህ የተባለው የቀድሞው የኩባ ፕሬዝዳንት የፊደል ካስትሮ ወንድም ራውል ካስትሮ ስልጣን ሊለቁ መሆናቸው መሰማቱን ተከትሎ ነው።
የሃገሪቱ ፓርላማም የራውል ካስትሮ ቀኝ እጅ ናቸው የተባሉትን ሜግዌል ዲያዝ ኬኔልን በምትካቸው መምረጡ ተሰምቷል።
የፊደል ካስትሮ ወንድም ራውል ካስትሮ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2006 ጀምሮ የኩባን የመሪነት ስልጣን ተቆጣጥረው ቆይተዋል።
የሃገሪቱን ኮሚኒስት ፓርቲንም ላለፉት 12 አመታት የመሩት ራውል ካስትሮ ታዲያ ከነዚህ አመታት የስልጣን ቆይታ በኋላ መንበሩን ለሌላ ሊያስረክቡ መዘጋጀታቸው ነው የተሰማው።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ የራውል ካስትሮ ቀኝ እጅ ናቸው የሚባሉት ሜግዌል ዲያዝ ኬኔል መንበረ ስልጣኑን እንዲረከቡ በሃገሪቱ ፓርላማ ተመርጠዋል።
የሜግዌል መመርጥ ደግሞ ለረጅም አመታት በፊደል ካስትሮ ቤተሰብ ስር የነበረው የስልጣን ቆይታ እንዲያከትም ያደርገዋል ተብሏል።
ነገር ግን ተመራጩ ፕሬዝዳንት የራውል ካስትሮ ቀኝ እጅ በመሆናቸው ምናልባትም በሚወስኑት ማንኛውም ውሳኔ ውስጥ የራውል ካስትሮ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊኖርበት ይችላል የሚሉ ግምቶችም በመንጸባረቅ ላይ ናቸው።
በሀገሪቱ ፓርላማ የተሾሙት አዲሱ መሪ የኩባን ኢኮኖሚ የማስተካካል በተለይ ለወጣት ኩባውያን የስራ እድል የመፍጠር ትልቅ ሃላፊነት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።
ዘገባው እንዳለው ከሆነ ደግሞ ራውል ካስትሮ ከሀገሪቱ መንበረ ስልጣን ይልቀቁ እንጂ እስከ 2021 ድረስ የፓርቲያቸው መሪ ሆነው ይቀጥላሉ።