(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 9/2010) አቶ በቀለ ገርባ የሰላም ጠንቅ የሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአስቸኳይ እንዲያነሱ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መልዕክት አስተላለፉ።
በቅርቡ ከእስር የተፈቱት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በግላቸው ባስተላለፉት በዚሁ መልዕክት ህዝቡ ለሰላም ዘብ ይቁም በማለት ብቻ ሰላም አይገኝም ብለዋል።
አቶ በቀለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ቢሮአቸው ተመልሰው በአራት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንዲሰጡም ጠይቀዋል።
አቶ በቀለ ገርባ መልዕክታቸውን የጀመሩት አባገዳ በየነ ሰንበቶ በቅርቡ የተናገሩትን በመጥቀስ ነው።
አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ “ሰላም ከፍ ባለ ድምጽ ተራራ ላይ ወጥቶ በመጥራት የሚገኝ አይደለም’’ ማለታቸውን የጠቀሱት አቶ በቀለ ገርባ ሰላም እንዳይኖር ያደረገው የኢህአዴግ አገዛዝ ነው።
ህዝቡማ ምንጊዜም ሰላም ወዳድና ሁሌም ሰላማዊ ነው ሲሉ በመልዕክታቸው አንስተዋል።
ህዝቡ ለሰላም ዘብ ይቁም ብሎ ጥሪ ማድረግ እምብዛም ቦታ የለውም ያሉት አቶ በቀለ ገርባ እውነተኛ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጽሕፈት ቤታቸው ተመልሰው ፣ ካቢኔአቸውን በመሰብሰብ ውሳኔ መስጠት ይገባቸዋል ብለዋል።
በዚህም አራት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ ነው በአቶ በቀለ ገርባ መልዕክት ውስጥ በዝርዝር የተገለጸው።
አቶ በቀለ ገርባ የቅድሚያ ተግባር ብለው ያስቀመጡት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ነው።
የሰላም ጠንቅ የሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳት የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስቸኳይ ውሳኔ የሚፈልግ ጉዳይ እንደሆነም ገልጸዋል።
አቶ በቀለ ገርባ የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን በሙሉ መፍታትንም በሁለተኛ ደረጃ አንስተዋል።
የህዝቡን የልብ ትርታ ለማየት የፖለቲካ እስረኞችን በችርቻሮ መፍታትን በማቆም ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ትዕዛዝ ማስተላለፍ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጠበቅ ውሳኔ እንደሆነ አቶ በቀለ ገርባ አጽንኦት በመስጠት ጠቅሰዋል።
ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት በጨለማ ቤቶች ውስጥ ታጉረው የሚሰቃዩ በኦነግ ስም የታሰሩ እንዳሉ የገለጹት አቶ በቀለ ገርባ እነዚህ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጠይቀዋል።
ሌላው በአቶ በቀለ ገርባ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተላለፈው መልዕክት ላይ የተጠየቀው የወታደሮች ወደካምፓቸው የመመለሳቸው ጉዳይ ነው።
በየመንደሩና በየከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ውስጥ ተበትነው ሰላም የሚነሱትን የመከላከያና የአጋዚ ወታደሮችን ወደ ካምፓቸው እንዲመለሱ ትእዛዝ እንዲያስተላልፉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል።
በመጨረሻም ከእውነተኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር እውነተኛ ድርድር ለማድረግ ለሁሉም በግልጽ ይፋዊ ጥሪ ማድረግ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ይጠበቃል ሲሉም የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ገልጸዋል።
እነዚህ አራት መሰረታዊ ጉዳዮች ትክክለኛ መልስ ካገኙ ህዝቡ ለሌሎች ጥያቄዎቹ መልስ ጊዜ ሊሰጥ ይችላል ብለዋል አቶ በቀለ ገርባ። ሰላም የሚመጣውም ያን ጊዜ ብቻ ነው።
ህዝብ ሰላም የሚያጣው ጦርነት ስላለ ብቻ አይደለም ያሉት አቶ በቀለ ገርባ የኢትዮዽያ ህዝብ ጦርነት ሳይኖር ሰላም አጥቶ ለዘመናት ኖሯል።
በተለይም በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመናት የሃገሪቱ ህዝብ ሌላው ቀርቶ የአእምሮ ሰላም ለማግኘት አልቻለም በማለትም ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በላኩት መልዕክት ላይ አጽኖት ሰጥተው ገልጸዋል።