በቡሌ ሆራ የተፈጸመውን ዘግናኝ ድርጊት የሰብአዊ መብት ድርጅቶች አጣርተው እርምጃ እንዲወስዱ ተጠየቀ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 09 ቀን 2010 ዓ/ም) ከሁለት ቀናት በፊት በጉጂ እና ጌዲዮ ማህበረሰብ አባላት መካከል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ ቆስለው በከተማው በሚገኝ ሆስፒታል የተጠለሉ ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው ያበሳጫቸው የሆስፒታሉ ሰራተኞች፣ በቁስለኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ ከኢትዮጵያ ባህል የወጣና ሰብአዊ መብትንም የሚጥስ በመሆኑ ገለልተኛ አካላት አጣርተው እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል። የሰብአዊ መብት ድርጅቶችም በጉዳዩ ላይ ትኩረት በመስጠት ድርጊቱ እንዲወገዝ እና የድርጊቱ ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።
4 ሰዎች ቆስለው ወደ ሆስፒታል በደረሱበት ወቅት፣ አንዳንድ ሰዎች ወደ ሆስፒታል ገብተው ቁስለኞቹን በእግራቸው በመርገጥ፣ በመደብደብና የተለያዩ ስብዕናን የሚነኩ ድርጊቶችን ሲፈጽሙባቸው እንደነበር የሚገልጹት የሆስፒታሉ ሰራተኞች፣ በግቢው የነበሩ ፖሊሶች እንዲህ አይነት ድርጊት ሲፈጸም በዝምታ ማየታቸው ይበልጥ እንዳናደዳቸው ተናግረዋል። የሆስፒታሉ ሰራተኞች ቁስለኞችን ወደ ውስጥ በማስገባት አልጋ ይዘው ህክምና እንዲያገኙ ቢያደርጉም፣ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች በሌሊት በመግባት 4ቱንም ሰዎች አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ገድለዋቸው መሄዳቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ሆስፒታል የገባ ሰው ሊገደል ቀርቶ ቀና ብሎ ሊታይ አይገባውም ያሉት ሰራኞቹ፣ ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩ የተፈጸመው ድርጊት ሊወገዝ እና አጥፊዎቹም ተገቢውን ቅጣት ሊያገኙ ይገባል ብለዋል።
ምንም እንኳ በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል የተነሳው ግጭት ዛሬ ጋብ ያለ ቢመስልም፣ በአገጠሩ አካባቢ አሁንም ከፍተኛ ግጭት መኖሩን ነዋሪዎች ገልጸዋል። አካላቸው የተጎዱ ቁስለኞች ህክምና ለማግኘት ከገጠር ወደ ከተማ እየገቡ ነው።
በቃርጫ ወረዳ የተጠለሉ ዜጎች ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንዳዳጋጠማቸው በተለይ እናቶችና ህጻናት በረሃብ እየተጠቁ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል። እስካሁን በተለያዩ ከተሞች ምን ያክል ሰዎች እንደተሰደዱ ባይታወቅም፣ በጎቲቲ፣ ጫልቤሳ፣ ገደብ፣ ጮርሶ በሚባሉ ቀበሌዎች እስከ 60 ሺ የሚደርሱ የጌዲዮ ተወላጆች ተፈናቅለዋል። በተለይ ጫልጫሌና ባያ በሚባሉ አካባቢዎች በርካታ ዜጎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የጌዲዮ ማህበረሰብ አባላት ከ1987 ዓም ጀምሮ በደቡብ እና ኦሮምያ ክልሎች ተከፍለው የሚኖሩ ሲሆኑ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በርካታ ግጭቶች ተከስተዋል።