የጣናን ደለል ለማውጣት ታስቦ የተገዛው ማሽን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 08 ቀን 2010 ዓ/ም) ወደ ጣና ሐይቅ በየዓመቱ የሚገባውን ከሰላሳ ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ አፈር ለማስወገድ ታስቦ ከሶስት ዓመት በፊት በሃያ ሚሊዮን ብር የተገዛው የደለል ማውጫ ማሽን ካለ አገልግሎት መቀመጡ ታወቀ፡፡
ወደ ሐይቁ የሚገባውን ግዙፍ ደለል ለማውጣት ታስቦ በ2007 ዓ.ም የተገዛው የደለል ማውጫ ማሽን ያለአገልግሎት በጐርጐራ ወደብ መቀመጡን የአባይ ተፋሰስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ የወንድወሰን መንግሥቱ ለመንግስት ሚዲያዎች አጋልጠዋል፡፡
በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውና ከጣናም አልፎ እንደ ቆጋ፣ ርብ፣ መገጭ፣…ለመሳሰሉት ግድቦች ደለል ማውጫ ይሆናል ተብሎ የተገዛው ማሽን ያለአገልግሎት የተቀመጠው ማሽኑን የሚጐትት ጀልባ አብሮ ባለመቅረቡ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ማሽኑ ወደ ስራ ባለመግባቱ ምክንያት በጣና ሐይቅ የሚከሰተው ደለል ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ለመንግስት ጋዜጠኞች የገለጹት አቶ የወንድወሰን በቀጣይም የሚቻለውን ሁሉ አድርገው ማሽኑን ወደ ስራ ለማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በችግርነት እንደተጋረጠባቸው ጠቁመዋል፡፡