(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 5/2010) ዩጋንዳ እስራኤል ከሃገሯ እንዲወጡ ካዘቸቻቸው ስደተኞች መካከል 500 የኤርትራና የሱዳን ስደተኞችን እቀበላለሁ አለች።
ዩጋንዳ ስደተኞቹን ለመቀበል የወሰነችው እስራኤል በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞችን ከሃገር አባርራለሁ ማለቷን ተከትሎ ነው።
እስራኤል በሃገሯ የሚኖሩ አፍሪካውያን ስደተኞችን አስወጣለሁ ስትል ቆይታለች።
ይህን ተከትሎም ዩጋንዳ እስራኤል ከሃገር ከምታስወጣቸው አፍሪካውያን መካከል 500 ያህል የሚሆኑ የኤርትራና የሱዳን ስደተኞችን ተቀብላ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች።
ጥሪውን በስደተኞች ተወካዩ ሙሳ ኢኩዌሩ አማካኝነት አስተላልፋለች።
እንደ ሙሳ ገለጻ ከሆነ በእስራኤል ጥገኝነት በመጠየቅ ላይ የነበሩትንና ወደ ዩጋንዳ ለመምጣት ፈቃደኛ የሆኑትን ዜጎች ሃገራችን ዩጋንዳ ትቀበላለች ብለዋል።
ወደ ዩጋንዳ የሚመጡትም ስደተኞች ያቀረቡት የጥገኝነት ጥያቄ ምንድነ ነው የሚለውንና ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውንም እናጣራለን ሲሉ ተናግረዋል።
ወደ ዩጋንዳ ሲመጡም መኖር የሚፈልጉበትን ቦታ እንዲመርጡ ይደረጋል ነው ያሉት።
በአለም ላይ በራቸውን ለስደተኞች በራቸውን ክፍት ካደረጉት ሃገራት መካከል ዩጋንዳ የምትጠቀስ ሲሆን 1 ነጥብ 4 ሚሊየን የጎረቤትና ራቅ ካለ ስፍራም የመጡ ስደተኞች እንደሚኖሩባትም ቢቢሲ በዘገባው ላይ አስፍሯል።