የዋልድባ መነኮሳት ከእስር ተፈቱ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 5/2010) የዋልድባ መነኮሳት ከእስር ተለቀቁ።

መነኮሳቱን ጨምሮ 114 የሕሊና እስረኞች ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል።

አቃቤ ሕግ የ114 የሕሊና እስረኞች ክስ እንዲቋረጥ ያደረገው ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ነው።

ክሱ እንዲቋረጥ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ያስታወቀው አቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ለሚገኙበት ለቂሊንጦ እስር ቤት የመፍቻ ትዕዛዝ እንዲጻፍለት ጠይቋል።

በዚሁም መሰረት ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ሁለቱን የዋልድባ መነኮሳት ጨምሮ 114ቱም የሕሊና እስረኞች ዛሬ አርብ ሚያዚያ 5/2010 ቀትር ላይ ከእስር ተፈተዋል።

መነኮሳቱ አባ ገብረኢየሱስ ኪዳነማርያም ካሴ እና አባ ገብረስላሴ ወልደሃይማኖት ከእስር ከተለቀቁ በኋላ መልዕክት አስተላልፈዋል።

“ከእኛ ጋር በመከራ ሰአት ከጎናችን ያልተለያችሁ፣ድምጻችንን ለአለም ሕዝብ ያስተላለፋችሁ በሙሉ ልኡል ፈጣሪ ውለታችሁን ይክፈላችሁ”በማለት ጥያቄያችን መልስ እስከሚያገኝም አትለዩን ብለዋል።

እኛ ብንፈታም የታሰርንበት አላማ አልተፈታም ነው ያሉት።

ሁለቱ መነኮሳት በዋልድባ አካባቢ የስኳር ፋብሪካ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ከተጀመረበት 2004 ጀምሮ የገዳሙን ይዞታ ለማስከበር ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።