(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 5/2010) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከትግራይ ልዩ ልዩ ወረዳዎች ከተውጣጡ ሰዎች ጋር በመቀሌ ከተማ ውይይት አደረጉ።
ዶክተር አብይ አህመድ በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግር የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ መሰረት ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ መቀሌ ያመሩት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ተቃዋሚዎች ጋር በቤተመንግስት የራት ግብዣ ካደረጉ በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ መቀሌ ካመሩ በኋላ የሰማዕታት ሃውልት ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ በሕወሃት ትግል ወቅት ለተሰው ታጋዮች የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።
የሕሊና ጸሎትም አድርገዋል።ከትግራይ የተለያዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ ሰዎች በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግርም የትግራይ ሕዝብ ሀገሩን የሚወድና ጨቋኝ ገዥዎችን ሲታገል የቆየ መሆኑን አስታውሰዋል።
የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር በመሆን ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት ልጆቹን ገብሯልም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከመቀሌ መለስ በመጪው ዕሁድ ከ25 ሺ በላይ ወጣቶችንም በአዲስ አበባ በሚሊኒያም አዳራሽ ያወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በመጪው ሰኞ ደግሞ በሼራተን አዲስ ሆቴል ከባለሃብቶችና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለመነጋገር መርሃ ግብር ይዘዋል።ከዚያም በባህርዳርና በጎንደር ተገኝተው ተመሳሳይ ጉብኝት ያደርጋሉ።በባህርዳር በአንድ ቀን 50 ወጣቶች በተገደሉበት ስፍራ ሃዘናቸውን በመግለጽ ይቅርታ ይጠይቃሉም ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ መቀሌ ከማምራታቸው በፊት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች በቤተመንግስት የራት ግብዣ አድርገዋል።
በዚሁ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም ካለጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ የዲሞክራሲ ግንባታ የትም አይደርስም ብለዋል።
እናም ኢሕአዴግ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
ድርጅታቸው ኢሕአዲግ ሰላማዊ ትግልን ምርጫቸው ካደረጉ ማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በቅርቡ ከእስር የተፈቱት አቶ በቀለ ገርባና ዶክተር መረራ ጉዲና እንዲሁም የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል የነበሩት የቀድም የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ ፣ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ እና ሌሎችም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የራት ግብዣ ላይ ተገኝተዋል።