በኢትዮ-ሶማሊ ክልል በደረሰው የጎርፍ አደጋ በርካታ ዜጎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተዘገበ

በኢትዮ-ሶማሊ ክልል በደረሰው የጎርፍ አደጋ በርካታ ዜጎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተዘገበ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 03 ቀን 2010 ዓ/ም) ባለፈው ቅዳሜ ጭናክሰን ከሚባል የምስራቅ ሃረርጌ አካባቢ የተነሳ ጎርፍ፣ በርካታ የጅግጅጋ ነዋሪዎችን ለሞት መዳረጉን ወኪላችን ገልጾአል።
በተለይ በጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ አካባቢ በሚገኘው ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ዙሪያ ሰፍረው የሚገኙ ዜጎች በአካባቢው ከሚገኘው የቆሻሻ ክምር ጋር ተደባልቀው በጎርፍ መወሰዳቸውን ዘጋቢያችን ገልጿል። የሟቾቹን አስከሬን ለማፈላለግ ወላጆችና ዘመዶች ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆኑ፣ አንዳንድ አስከሬን እስከ 200 ኪሜ የሚደርስ እርቀት መወሰዱን ዘጋቢያችን ገልጿል። ምንም እንኳ የሟቾችን ቁጥር በትክክል ለማወቅ ባይቻልም፣ እስከ 50 የሚደርሱ ነዋሪዎች እንደጠፉ የአካባቢው ነዋሪዎች እየተናገሩ መሆኑን ዘግቧል።
አደጋው የደረሰው ባለፈው ቅዳሜ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ጅግጅጋን በጎበኙበት ወቅት ሲሆን፣ የክልሉ አስተዳደር የደረሰውን ጉዳት እስካሁን ይፋ ለማውጣት እንዳልፈለገና ዜጎችን ለመርዳት ምንም አይነት ጥረት እያደረገ እንዳልሆነ የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።