የአያንቱ መሃመድ ሳዶ የቀብር ስነስርአት ተፈጸመ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 2/2010)በኦሮሚያ ክልል በአንድ የታጠቀ ወታደር የተገደለችው አያንቱ መሃመድ ሳዶ የቀብር ስነስርአት ተፈጸመ።

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቆቦ ከተማ በአገዛዙ ወታደሮች ታግታ የተገደለችው ነፍሰጡር ሴት የአንድ ሴት ልጅ እናትም ነበረች።

ወታደሩ እኩለ ሌሊት ላይ ነፍሰጡር ሴቷን አግቶ የገደለበትን ምክንያት ሰውየው ታስሮ እየተጣራ ነው ተብሏል።

ጫላ ኢብራሒም በከሬ በነፍሰጡር ሴቷ ላይ ግድያ የፈጸመው ወታደር ነው።

አያንቱ መሃመድ ሳዶ የተባለችው ነፍሰጡር ስራ አምሽታ ወደ ቤቷ በማምራት ላይ እያለች በአገዛዙ ወታደሮች ከታገተች በኋላ ወደአልታወቀ ስፍራ ሊወስዷት ሲሉ ፈቃደኛ ባለመሆኗ ግድያው ሊፈጸምባት ችሏል።

አያንቱ የ4 አመት እድሜ ያላት ሴት ልጅ እናት ስትሆን ከዚህም አልፎ የ3 ወር ነፍሰጡርም ነበረች ተብሏል።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሃረርጌ ቆቦ ከተማ ግድያው ከተፈጸመ በኋላ ጫላ ኢብራሒም በከሬ የተባለው የአገዛዙ ወታደር በቁጥጥር ስር ውሏል።

በግድያው የተባበሩት የአገዛዙ ታጣቂዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።

በታጠቁ የመንግስት ሃይሎች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችው አያንቱ የቀብር ስነስርአትም ጋንዲ ቱቻ በተባለ የመቃብር ስፍራ ዛሬ የተፈጸመ መሆኑ ታውቋል።

በቀብር ስነስርአቱ አመጽ ሊቀሰቀስ ይችላል በሚልም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት አካባቢውን ከቦ እንደነበረም የአዲስ ስታንዳርድ ዘገባ አመልክቷል።

እንደ ዘገባው የፌደራል ፖሊስ አባላት አካባቢውን በመውረራቸው በከተማዋ ከፍተኛ ፍርሃትና ስጋት ተፈጥሯል።

ቆይቶ በደረሰን ዘገባ ደግሞ ድርጊቱን ተከትሎ በቆቦ የሕዝብ ተቃውሞ ተቀስቅሷል።

የአያንቱን ግድያ በተመለከተ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፖሊስ ድርጊቱ በመከላከያ ሰራዊት ባልደረባ መፈጸሙን ገልጾ የድርጊቱ ፈጻሚም ሆነ ተባባሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።