ኤች አር 128 የተባለው ረቂቅ ሕገ ደንብ ዛሬ ድምጽ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 2/2010)ኤች አር 128 የተባለው ረቂቅ ሕገ ደንብ ዛሬ በአሜሪካ ምክርቤት ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገለጸ።

ይሄ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ረቂቅ ሕገ ደንቡ ስለመጽደቅና አለመጽደቁ የታወቀ ነገር የለም።

ዛሬ ከሰአት በኋላ በአሜሪካ ምክር ቤት የሚቀርበው ይህ ረቂቅ ህገ ደንብ ከአንድ መቶ በላይ የምክር ቤቱ አባላት የደገፉት መሆኑም ታውቋል።

በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት እንዲከበርና ሁሉንም የሳተፈ መንግስታዊ ስርአት እንዲኖር ለማበረታታት በሚል የተረቀቀው ኤች አር 128 በሀገሪቱ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳትን ጨምሮ ልዩ ልዩ መሰረታዊ ድንጋጌዎችን ይዟል። በስልጣን ላይ ያሉ ተጠያቂ ሰዎች ሃብታቸው እንዲታገድና አሜሪካ እንዳይገቡም ይከለክላል።

የፖለቲካ መሪዎች፣ጋዜጠኞች፣የመብት ተሟጋቾች በአጠቃላይ የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቀው ረቂቅ ሕግ፣በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን ለመመርመር የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ራፖርተሮች እንዲገቡም ይጠይቃል።

ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብታቸው እንዲከበር የመሰብሰብና የመደራጀት መብታቸው እንዲጠበቅም ረቂቅ ሕገ ደንቡ ያሳስባል።

በኢትዮጵያ የሚፈጸመው ግድያ በተለይም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር መስከረም 3/2016 እንዲሁም ጥቅምት 2/2016 በቂሊንጦ ወህኒ ቤት የተነሳው ቃጠሎና ግድያ በእሬቻ በአል ላይ የተፈጸመውን እልቂት የተባበሩት መንግስታት ባለሙያዎች ገብተው እንዲመረምሩት ይጠይቃል።

በሰብአዊ ረገጣ ተጠያቂ የሆኑ ባለስልጣናት በአሜሪካን ሀገር ገንዘብና ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ እንዲሁም ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ገደብ እንደሚጣልባቸውም መረዳት ተችሏል።

ይህ ኤች አር 128 የተባለው ረቂቅ ሕገ ደንብ በአሜሪካ ሰአት አቆጣጠር ዛሬ ከሰአት በኋላ በአሜሪካው ሕግ አውጭ ምክር ቤት በካፒቶል ሒል ይቀርባል ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን ይሄ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ረቂቁ አልቀረበም።