10 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በሞቃዲሾ አውሮፕላን ማረፍያ ተያዘ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 1/2010) ንብረትነቱ የማን እንደሆነ ያልታውቀ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ሞቃዲሾ አውሮፕላን ማረፍያ ተያዘ ።

ገንዘቡ ከዩናይትድ አረብ ኤምሬት መዲና አቡዳቢ  ወደ ሞቃዲሾ በበረረ አውሮፕላን ውስጥ መገኘቱ  በሃገራቱ መካከል ውጥረት አስከትሏል።

ዩናይትድ አረብ ኤምሬት  ከሶማሌ ላንድ መንግስት ጋር በርበራ ወደብ ላይ ያደረገችው ስምምነት  የሶማሊያን መንግስት ማስቆጣቱ ይታወሳል።

በዚህም የሶማሊያ መንግስት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሉዓላዊነቴ ተደፍሯል በማለት የተባበሩት አረብ ኤምሬትን መክሰሱ ይታወቃል።

በሮያል ጄት አውሮፕላን ከአቡዳቢ ተነስቶ ትናንት ዕሁድ  ሞቃዲሾ  አውሮፕላን ማረፊያ የደረሰው ገንዘብ  በሶስት ቦርሳዎች የታጨቀ ሲሆን ፣አጠቃላይ ድምሩ 9.6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው።

አልጀዚራ እንደዘገበው ቦርሳዎቹ ስም አልተጻፈባቸውም  የማን እነደሆኑ የሚገልጽ ምንም ምልክትም አልተገኘባቸውም።

ገንዘቡ በትክክል ከየት እንደመጣ እና ለማን ሊሰጥ እንደተዘጋጀ  በሶማሊያ  የጸጥታ ሰራተኞች ምርመራው መቀጠሉን የሶማሊያ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ገልጸዋል።

9.6 ሚሊየን ዶላር የያዘው ቦርሳ መገኘት በዩናይትድ አረብ ኤምሬት ኤምባሲ ሰራተኞች እና በሞቃዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ  ሃላፊዎች መካከል  ለሰዓታት  የዘለቀ አለመግባባት  ማስከተሉም ተመልክቷል።

የገልፍ ሃገራትን ቀውስ ተከትሎ በመጣው  ውዝግብ ገለልተኛ አቋም በመያዝዋ  ከሳውዲ አረቢያ እና ዩናይትድ ኤምሬት ጋር  ግንኙነትዋ የሻከረው ሶማሊያ ፣በበርበራ ወደብ ሳቢያ ደግሞ ከዩናይትደ አረብ ኤምሬት ጋር በግልጽ ውዝግብ ውስጥ መግባትዋ ይታወቃል።

የሶማሊያ አካል የነበረችው ሶማሌ ላንድ የዚያድባሬ መንግስት እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በጥር 1991 ሲወገድ ነጻነትዋን አውጃለች።

በዲሞክራሲያዊ ምርጫ መሪዎችዋን እየለዋወጠች ቢሆንም አለም አቀፍ ዕውቅና ግን አላገኘችም።

ከዚህች ዕውቅና ከሌላት ሃገር ጋር የዩናይትደ አረብ ኤምሪት መንግስት በበርበራ ወደብ ላይ የፈጸመው የ30 ዓመታት ውል የሶማሊያን መንግስት በማስቆጣቱ ጉዳዩን ወደተባበሩት መንግስታት መውሰዱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ መንግስትም ዋነኛው የወደቡ ተጠቃሚ በመሆኑ ጥቂት የባለቤትነት ድርሻ ማግኘቱንም የሶማሊያ መንግስት ተቃውሟል።