ስቃይ ሲፈጸምባቸው የነበሩ ግለሰቦች ምስክርነታቸውን ሰጡ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 1/2010)  በሕወሐት መራሹ አገዛዝ በማእከላዊ ምርምራ እስር ቤት  ስቃይ ሲፈጸምባቸው የነበሩ ግለሰቦች ለመንግስት መገናኛ ብዙሀን ምስክርነታቸውን ሰጡ።

ማእከላዊ ለሰው ልጅ ሕሊና የሚከብድና ዘር እስከማጥፋት የሚደርስ እርምጃ በዚህ መንግስት ሲወስድበት እንደነበር የችግሩ ሰለባዎች ገልጸዋል።

ባለፉት 26 አመታት በማዕከላዊ ምርመራ እስር ቤት ከፍተኛ ስቃይ ሲፈጸምባቸው የነበሩ ግለሰቦች ምስክርነታቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለሆነው የኦሮሞ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ/ኦ ቢ ኤን/ ገልጸዋል።

ለሚዲያ ተቋሙ አስተያየታቸውን የሰጡት ግለሰቦች ማዕከላዊ ለሰው ልጅ ሕሊና የሚከብድና አስከፊ እንደሆነ ተናግረዋል።

በ2000 አመተ ምሕረት በማዕከላዊ ምርመራ ውስጥ ግፍ የተፈጸመበት መሆኑን የገለጸ አንድ ወጣት “ዛሬ ስለ ማዕከላዊ ሳወራ ከአስር አመት በፊት ማዕከላዊ ስለነበርኩ ነው።

አሁንም ስሜቱ አለቀቀኝም።የሰው ልጅ ከማዕከላዊ ወጥቶ ስለ ነገ ሕይወቱ እንኳን እንዳያስብ  ሊሆን ይችላል።እስከመሞትም ሊደርስ ይችላል” በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል።

በማዕከላዊ ቆይታው ከፍተኛ ግፍ የተፈጸበት ሌላ ወጣት”በሰው ልጅ ላይ ሊፈጸም የማይገባው ዘግናኝ በደል ተፈጽሟል።

ከአነስተኛ ግርፋት ጀምሮ የሰው ሕይወት ወይም ዘር እስከማጥፋት የሚደርስ በደል ሲፈጸም ነበር።” በማለት የአይን ምስክርነቱን ሰጥቷል።

በማዕከላዊ ከፍተኛ ምርመራ የተደረገባቸው የሜጫና ቱለማ መረዳጃ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ድርቢ ደምሴ በበኩላቸው ሰዎች ከዚያ ከወጡ በኋላ በትክክል አይኖሩም።

አብዛኞቹ ታመው ይሞታሉ።–አልያም ደግሞ ያብዳሉ።

በቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰው ችግር ከዚህ በላይ ነው ብለዋል።

ሕወሃት/ኢሕአዴግ ማዕከላዊን ለመዝጋት የወሰነው በደርግ ዘመን ሰቆቃና ግፍ ሲፈጸምበት በመኖሩ በሕብረተሰቡ ዘንድ መጥፎ ስሜት ስለፈጠረ  ነው ማለቱ ይታወሳል።