(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 28/2010) ምስራቅ አፍሪካ ለሁለት ልትሰነጠቅ እንደምትችል አንድ ጥናት አመለከተ ጥናት አመለከተ።
እንደ ጥናቱ ከሆነ በደቡብ ምዕራብ ኬንያ ብዙ ኪሎ ሜትርን የሚሸፍን መሬት ለሁለት ተገምሷል።
የመሬቱ ለሁለት መገመስም ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንና ስጋት ማጫሩን ነው ዘገባዎች ያመለከቱት።
የስምጥ ሽለቆን ተከትሎ 3000 ኪሎ ሜትር ይደርሳል የተባለውና ከምስራቅ አፍሪካ እስከ ዚምባቡዌ ይደርሳል የተባለው የመሬት መሰንጠቅ አፍሪካን ለ2 እኩል ያልሆነ ቦታ ይከፍላታል የሚል ስጋት መኖሩ ነው መረጃዎች ያመለከቱት።
እንደ ሲ ኤን ኤን ዘገባ ከሆነ በደቡብ ምዕራብ ኬንያ የተከሰተው የመሬት መሰንጠቅ የስምጥ ሸለቆን ተከትሎ ከፍተኛ የመሬት መሰንጠቅ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ነው የተነገረው።
ከዚህ ቀደም የተደረጉ ተከታታይ ጥናቶች እንደሚጠቁሙትም የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሽለቆ ውስጥ አለ ከሚባለው እሳተጎሞራ ጋር በተያያዘ የምስራቃዊው የአፍሪካ ክፍል የመከፈል አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል።
በዚህም ኢትዮጵያን ጨምሮ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳና ኬንያ በዋናነት ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉ ሲል ዘገባው አመልክቷል።
የመሬት መሰንጠቅ አደጋው ወደ ዚምባቡዌ እየተስፋፋ ሊሄድ እንደሚችል ጥናቱ አመልክቷል።
በኬንያ ደረሰ የተባለው ይህው የመሬት መሰንጠቅ አደጋ በስፍራው ያሉ ነዋሪዎችን ማፈናቀሉን እና መጠኑም ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱ ነው የተነገረው።