(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 28/2010)በኢትዮጵያ፣በግብጽና በሱዳን መካከል በካርቱም የተካሄደው ውይይት ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ታወቀ።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለዜና ሰዎች እንደገለጹት በርካታ ጉዳዮች ላይ ውይይት ቢደረግም በአንድም ጉዳይ ላይ ከስምምነት ሳይደረስ ስብሰባው ተጠናቋል።
ከ7 አመት በፊት የተገነባው የሕዳሴው ግድብ በግርጌ ባሉ ሃገራት ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ በተመለከተ በፈረንሳይ ኩባንያ የተደረገውን ጥናት ለማጽደቅ ሃገራቱ ሳይስማሙ ቆይተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የውሃ ሚኒስትሮች እንዲሁም የደህንነት ባለሙያዎች በተገኙበት ዕረቡ እለት በካርቱም የተጀመረው ስብሰባ እስከዛሬ አርብ ማለዳ የቀጠለ ቢሆንም በስተመጨረሻ ግን ያለውጤት መጠናቀቁ ነው የተገለጸው።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስብሰባው ያለውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ “ለበርካታ ሰአታት በብዙ ጉዳዮች ላይ የተወያየን ቢሆንም ወደ ስምምነት ማምራት ግን አልተቻለም’’ ብለዋል።
ሆኖም ያልተሰማሙባቸው ጉዳዮች ግን ከማብራራት ተቆጥበዋል።
ያለውጤት የተጠናቀቀው ውይይት በ30 ቀናት ውስጥ እንደገና እንዲቀጥል መስማማታቸውን የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሻሚ ሽኩር ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
አጠቃላይ ውይይቱ 15 ሰአታት የፈጀ እንደነበርም ተናግረዋል።