በማዕከላዊ እስር ቤት የሚገኙ እስረኞች ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተዛወሩ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 28/2010) በማዕከላዊ እስር ቤት የሚገኙ እስረኞች ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጊዜያዊ ማቆያ እንዲዛወሩ ተደረገ።

የእስረኛ ጠያቂዎች ከዛሬ ጀምሮ ወደ ማዕከላዊ እንዳይመጡ የሚገልጽ ማስታወቂ በእስር ቤቱ አጥር ላይ መለጠፉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጊዜያዊ ማቆያ ከተዛወሩት መካከል የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ ቃል አቀባይ አቶ ታዬ ደንደአ እና መምህር ስዩም ተሾመ እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል።

የአገዛዙ ልሳን የሆነው ሬዲዮ ፋና ማዕከላዊ እስር ቤት ተዘጋ ሲል ዛሬ በዘገባው ላይ አስፍሯል።

ማዕከላዊ እስር ቤቱ ተዘጋ ይባል እንጂ በተደራጀና ዘመናዊ በሆነ ሕንጻ ውስጥ ምርመራው የሚቀጥል መሆኑን መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል።

የአገዛዙ ልሳን የሆነው ሬዲዮ ፋና እንደዘገበው ማዕከላዊ እስር ቤቱ ከዛሬ ጀምሮ ተዘግቷል።

ወደ ማዕከላዊ ለጥየቃ የሄዱ የእስረኛ ቤተሰቦች ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንዲያመሩ እንደተነገራቸው ለማወቅ ተችሏል።

በእስር ቤቱ አጥር ላይም ከዛሬ 28/07/2010 ጀምሮ የህግ ተጠርጣሪዎችን ለመጠየቅ ለምትመጡ ጠያቂዎች አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሚገኘው ጊዜያዊ ማቆያ መጠየቅ ትችላላችሁ የሚል ማስታወቂያ ተለጥፎ እንደሚታይም ታውቋል።

ሬዲዮ ፋና እንዳለው ማዕከላዊ ይሰጥ የነበረውን እስረኞችን የማቆየትና የመመርመር አገልግሎትም ከዛሬ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ቆሟል።

ባለፉት 27 ዓመታት የህወሀት አገዛዝ በፖለቲካ ልዩነት የሚከሳቸውን ኢትዮጵያውያንን እስከህይወት መጥፋት በደረሱ ማሰቃየቶች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽምበት የነበረውን የማዕከላዊ የማሰቃያ (ቶርቸር) ቤት እንዲዘጋ የተወሰነው የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው የካቲት ወር ላይ ያደረገውን ስበሰባ ተከትሎ ነው።

በወቅቱም በተሻለ ህንጻ ላይ ስራው እንደሚቀጥልም መገለጹ የሚታወስ ነው።

ሬዲዮ ፋና እንዳስታወቀውም ማዕከላዊ የቦታ ለውጥ አድርጎ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ ተዛውሯል።

ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ በማዕከላዊ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ቢሮዎችን በመልቀቅ ካዛንቺስ ወደሚገኘው አዲስ ቢሮ መዘዋወሩን ነው ሬዲዮ ፋና ያስታወቀው።

በማዕከላዊ የሚፈጸመው ማሰቃየት በተደራጀ ሁኔታ የሚከናወን በመሆኑ እንጂ በርካታ ስውር የማሰቃያ ቦታዎች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ።

በአዲስ አበባ ውስጥ ካዛንቺስን ጨምሮ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ስውር የደህንነት ቤቶች እንደሚገኙና ማሰቃየት እንደሚፈጸምባቸው በተለያዩ የመረጃ ምንጮች ተረጋግጧል።

ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ስውር ቦታዎች የሚፈጸሙ ከፍተኛ ማሰቃየቶችም እንዳሉ ተጠቂዎች በተለያዩ ጊዜያት ከሚሰጡት ምስክርነት ለመረዳት ተችሏል።

በተለይም በትግራይ ባዶ ስድስት በመባል በሚታወቅና ከመሬት በታች በሚገኝ የማሰቃያ ቦታ በርካታ የወልቃይት ተወላጆች ግፍና ስቃይ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ማዕከላዊ የቦታ ለውጥ አድርጓል የሚሉ ወገኖች የአገዛዙ ውሳኔ መርመራውና ሌሎች ተግባራት እንደማይቀጥሉ ዋስትና የሚሰጥ እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ።

በተለይም አሰቃቂ ስቃይ ከመፈጸም አንስቶ ህይወት እስከማጥፋት በሚደርስ ወንጀል ውስጥ የተሰማሩ የማዕከላዊ መርማሪዎችና ሃላፊዎች በህግ የሚጠየቁበት ሁኔታ ካልተፈጠረ የህንጻ ለውጥ ብቻውን ትርጉም የለውም ሲሉ ይገልጻሉ።

በማዕከላዊ ከሚፈጸሙ ግፍና ማሰቃየቶች መሃል ጥፍር በጉጠት መንቀል፣ የሰውነትን አካል በኤሌክትሪክ ሽቦ መተልተል፣ በጨለማ ቤት ውስጥ ለቀናት በስቃይ ማቆየት፣ በራቁት ገላ ግርፊያና ድብደባ መፈጸም ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው።