(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 28/2010) ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ 11 ታዋቂ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ትናንት ተፈቱ ።
በሌላ ዜና ከወር በላይ በመላ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ በቀር የተቋረጠው የኢንተርኔት የዳታ አገልግሎት ዛሬ መጀመሩ ታውቋል።
መጋቢት 16 ቀን 2010 በድጋሚ ታስረው የነበሩት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ አንዱአለም አራጌ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ አዲሱ ጌታሁን፣ ጦማሪ ዘላለም ወርቅአገኘሁ፣ ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን፣ ጋዜጠኛ በፈቃዱ ሃይሉ፣ ወ/ት ወይንሸት ሞላ፣ ስንታየሁ ቸኮልና ተፈራ ተስፋዬ ትናንት ተለቀዋል።
ታሳሪዎቹ በአስጨናቂ የእስር ሁኔታ ውስጥ ማለፋቸውም ሲዘገብ ቆይቷል።
በሌላ ዜና ከወር በላይ በመላ ሃገሪቱ ከአዲስ አበባ በቀር ተቋርጦ የነበረው የኢንተርኔት የዳታ አገልግሎት ዛሬ መለቀቁ ተሰምቷል።
በይበልጥም በኦሮሚያና በአማራ ክልል ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ የቆየው የእጅ ስልክ የዳታ አገልግሎት ዛሬ መለቀቁን በሃገር ቤት የሚገኙ የምብት አቀንቃኞች አረጋግጠዋል።