አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ሥር ለሰደደው የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጡ ይገባቸዋል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ አቀረበ

አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ሥር ለሰደደው የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጡ ይገባቸዋል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ አቀረበ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 21 ቀን 2010 ዓ/ም) አዲሱ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር አብይ አህመድ በመላው አገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋውንና ሥር የሰደደውን መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ለመፍታት ከሁሉም ነገሮች ቅድሚያ ሊሰጡት ይገባል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገልጿል።
የጠቅላይ ሚንስትሩን መመረጥ አስመልክቶ የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ ሳሊል ሼቲ ”ጠቅላይ ሚንስትር አብይና መንግስታቸው በኢትዮጵያ መሰረታዊና ተአማኒነት ያለው ሥር ነቀል የተሃድሶ ለውጦችን በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ቅድሚያ በመስጠት ተጨባጭ የሆኑ ተግባራዊ ለውጦችን በአፋጣኝ ሊያሰፍኑ ይገባል።” ብለዋል።
አገሪቷ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት የተለያዩ የዜጎችን ነጻነት የሚገድቡ ሕጎች ተግባራዊ ሆነዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩለት፣ ነጻነት እንዲሰፍን በሚጠይቅበት ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ወደ ስልጣን መጥተዋል።
አስቸኳይ አዋጁ እንደታወጀ እጅግ አስደንጋጭ ክስተቶች በአገሪቱ ተከስተዋል። የካቲት 24 ቀን 2010 ዓም በደቡባዊ ኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ በአገዛዙ ታጣቂዎች በተወሰደ ኢሰብዓዊ ጭፍጨፋ 12 ሰላማዊ ሰዎች ተገለው በርካቶች ቁስለኛ የሆኑበት ለአብነት ማሳይ ተደርጎ ይወሰዳል በማለት አምነሰቲ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ጠቃቅሷል።
በያዝነው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ የተለቀቁ 12 ታዋቂ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ተመልሰው እንዲታሰሩ ተደርገዋል። በተመሳሳይ ባህርዳር ከተማ 19 ሙሁራንም ታስረዋል።
”የሰላማዊ ዜጎች ግድያ፣ የፖለቲካ እስረኞችን ፈቶ ዳግም እንዲታሰሩ ማድረጉ አገዛዙ የገባውን የለውጥ ተሃድሶ ቃልኪዳን አጠያያቂ ያደርገዋል። የጠቅላይ ሚንስትሩ ሹመት በፓርላማው ሲጸድቅ ሁሉንም እስረኞች ካለምንም ቅድመ ሁኔታዎች በመፍታት፣ ሁሉንም አፋኝ ሕጎችን ማንሳት አለበት። በተለይም የጸረ ሽብር ሕግ፣ የበጎ አድራጎትና የማኅበራዊ ድርጅቶችን በማገድ የሚያፍኑ ሕጎችን በማንሳት ለሰብዓዊ መብት መከበር ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል።”ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ጸሃፊ ሳሊል ሼቲ አክለው ተናግረዋል።