(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 21/2010) ባለፈው እሁድ እንደገና ተይዘው ከታሰሩት ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ውስጥ አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ታሞ ሆስፒታል መግባቱ ታወቀ።
የአሜሪካው የጸሃፊያን ተቋም ፔን አሜሪካም እስራቱን በማውገዝ እነ እስክንድር ነጋ ይፈቱ ሲል ጥሪውን አቅርቧል።
እስክንድር ነጋን በመጥቀስ ፔን አሜሪካ እንደገለጸው 5 ሜትር በ8 ሜትር ስፋት ባለው እስር ቤት ውስጥ 200 ሰዎች ታጭቀው በአስከፊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።
ባለፈው እሁድ መጋቢት 16/2010 ከእስር ለተፈቱት ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወላጅ እናት ቤት በተዘጋጀ ግብዣ ላይ ተይዘው የታሰሩት 12 ሲሆኑ በአሰቃቂ እስር ቤት ውስጥ መሆናቸውም ታውቋል።
እስር ቤቱ ከመጣበቡ የተነሳ ለመተኛት እንኳን በተቸገሩበት ሁኔታ ውስጥ መገኘታቸውንም አስታውቀዋል።
ከታሳሪዎቹ ውስጥ አንዱአለም አራጌና ተመስገን ደሳለኝ የወገብ ሕመም ያለባቸው በመሆኑ ይበልጥ በስቃይ ውስጥ መሆናቸውንም ታሳሪዎቹን የጎበኙ አክቲቪስቶችና ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።
በጠባብና አስጨናቂ የእስራት ሁኔታ ውስጥ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ታሞ ወደ ጤና ጣቢያ የተወሰደ ሲሆን ሕመሙ በመባባሱ በሃኪሞች ትዕዛዝ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል መዛወሩን የቅርብ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
መቀመጫውን በአሜሪካ ኒዮርክ ያደረገው ፔን አሜሪካ ትላንት ባወጣው መግለጫ ደግሞ የእነ እስክንድር ነጋ ኢሰብአዊ አያያዝና እስራት በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ላይ የተሰነዘረ አስከፊ ጥቃት ነው ሲል ገልጾታል።
እስክንድር ነጋ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ 2012 ከፔን አሜሪካ የመጻፍ ነጻነት ሽልማት ማግኘቱንም በመግለጫው አስታውሷል።
እስክንድር ነጋ በየካቲት ወር በይቅርታ ተፈቶ መጋቢት 16/2010 እንደገና መታሰሩን የገለጸው ፔን አሜሪካ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ጦማሪያን ዘላለም ወርቅአገኘሁ፣ በፍቃዱ ሃይሉና ማህሌት ፋንታሁንም በተመሳሳይ መታሰራቸውን በመግለጫው ዘርዝሯል።
የሚገኙበት አስከፊ የእስር ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን እስክንድር ነጋን በመጥቀስ በመግለጫው ያሰፈረው ፔን አሜሪካ 5 ሜትር በ8 ሜትር ስፋት ባለው ክፍል ውስጥ 200 እስረኞች ታጭቀው እንደሚገኙም የእስክንድርን ቃል ዋቢ በማድረግ ገልጿል።
እስር ቤቱ በእስረኞች በመጨናነቁ ለመቀመጥም ሆነ ለመተኛት መቸገራቸውን እስክንድር ነጋ ገልጿል።
“እንዲህ አይነቱ አሰቃቂ ሁኔታ የትኛውንም ወንጀል በፈጸመ ሰው ላይ ሊከሰት አይገባውም” በማለት የተናገረው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ “ያለምንም ወንጀል በታሰርነው በእኛ ላይ ጭምር ይህ አሰቃቂ ሁኔታ እየተፈጸመ ነው ብሏል። በመሆኑም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጉዳዩን እንዲያውቀውና ስቃያችን እንዲያበቃ የሚችለውን ሁሉ ያድርግ” ሲል መጠየቁን ፔን አሜሪካ ትላንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
መቀመጫውን በኒዮርክ አሜሪካ ያደረገው የጸሃፊያን ተቋም ፔን አሜሪካ እስክንድር ነጋና ሌሎቹም እስረኞች በአስቸኳይ ይፈቱ ሲል በዚሁ መግለቻው ጥሪውን አቅርቧል።