የቦትስዋናው ፕሬዝዳንት ስልጣን ለቀቁ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 21/2010) የቦትስዋናው ፕሬዝዳንት አያን ከሃን ስልጣን መልቀቃቸው ተሰማ።

የሁለት ዙር ስልጣናቸውን ሊያጠናቅቁ ጥቂት ጊዜ የቀራቸው ፕሬዝዳንት አያን ካሃን  መንበረ ስልጣኑን ቀድመው መልቀቅ የፈለጉት ለሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት በማሰብ ነው ተብሏል።

ፕሬዝዳንቱ በሀገሪቱ በሚገኙት 57 ግዛቶችም በመዘዋወር ስንብት አድርገዋል።

ካለፈው ታህሳስ ጀምሮ በሀገሪቱ በሚገኙ 57 ግዛቶች የስንብት ጉብኝት ያደረጉት  የቦትስዋናው ፕሬዝዳንት አያን ከሃን የስልጣን ዘመናቸውን ለመጨረስ 18 ወራት እንደሚቀራቸው ነው ዘገባዎች ያመለከቱት።

ፕሬዝዳንት አያን ከሃን በሃገሬ ሰላማዊ ሽግግር ሊኖር ይገባል በሚልም አስቀድመው መንበረ ስልጣኑን ማስረከባቸው ተሰምቷል።

በቦታቸውም ሌላ ፕሬዝዳንት እስኪተካ ድረስ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሃገሪቱን የማስተዳደሩን ሃላፊነት እንደሚረከቡ ታውቋል።

በሁለት ዙር የስልጣን ዘመናቸው ስኬታማ እንደነበሩ የተነገረላቸው ኢያን ከሀማ ስልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ በሃገሪቱ የነበረውን የስራ አጥ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ከነጻነት በኋላ የመጀመሪያው የቦትስዋና ፕሬዝንዳንት ስር ከሀማ ልጅ የሆኑት የ 67 አመቱ አያን ከሃማ ፓይለት የነበሩና በመከላከያ ሰራዊት ውስጥም ሀገራቸውን ያገለገሉ መሆናቸው ታውቋል።

የስልጣን ዘመናቸው ሳይጠናቀቅ ስልጣን ለመልቀቅ የወሰኑትም ለሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ብሎም ለሰላማዊ ሽግግር እንዲረዳ በማሰብ መሆኑ ተገልጿል።

አያን ከሀማ በዜጎቻቸው ዘንድ እውነተኛና ግልጽ ናቸው በመባል የሚወደዱ መሆናቸውን ዘገባዎች አመልክቷል።