የአፋርና የኦሮሞህ ህዝብ ለማጋጨት የተደረገውን ሙከራ ኦነግና አነግፓ አወገዙ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 20 ቀን 2010 ዓ/ም) የኣፋር ነጻነት ግንባር ፓርቲና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ባወጡት መግለጫ፣ የኢሕኣዴግ ሃይሎች እራሳቸውን በመደበቅ በምስራቅና ሰሜን-
ምስራቅ የኦሮሚያና የኣፋር ክልል ኣዋሳኝ ድንበር ላይ በሰላማዊ መንገድ ኑሮኣቸውን ሲመሩ በነበሩ ሲቪሎች ላይ ጥቃት ሊያደርሱ መሞከራቸውን ጠቅሰዋል። ድርጊቱ የወያኔ/ኢሕኣዴግ ስርዓት በመላው ሃገሪቷ ብሄሮችና ብሄረሰቦችን ለማናቆር ሲፈጽመው የነበረው ድራማ አካል ነው ሲሉ ድርጅቱ አስታውቀዋል።
እድሜው ኣልቆ ከመቀበሪያው ኣፋፍ የሚገኘው ኣምባገነን ስርዓት ተስፋ በመቁረጡ፡ ቡድኑን ስልጣን ላይ ለማቆየት ሲል ማንኛውንም ኣይነት ወንጀል ከመፈጸም ወደኋላ ኣይልም ያሉት ድርጅቶቹ፣ የኣፋር ህዝብ፣ የኦሮሞ ህዝብና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሌሎችም ህዝቦች የሕወሃት/ኢሕኣዴግ መንግስት በመካከላቸው የሚሸርበውን ሴራ በንቃት በመጠበቅ፡ ስርዓቱ የሚፈጥራቸውን ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ መልዕክት እናስተላልፋለን ብለዋል።