ዶ/ር አብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው በመመረጣቸው የተለያዩ አስተያየቶች እየቀረቡ ነው
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 19 ቀን 2010 ዓ/ም) ኢህአዴግ ለሳምንታት ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ በመጨረሻም የኦህዴድ ሊ/መንበር የሆኑትን ዶ/ር አብይ አህመድን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡን ይፋ አድርጓል። የህወሃት ደጋፊ የመገናኛ ብዙሃን ዶ/ር አብይ እንዳይመረጥ ከፍተኛ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ቢከርሙም በመጨረሻ ዶ/ር አብይ ተመርጠዋል። ዶ/ር አብይ እንዲመረጡ ብአዴን ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተም ታውቋል።
የዶ/ር አብይን መመረጥ ተከትሎ ከፍተኛ ተስፋ ያሳደሩ በርካታ ዜጎች በፌስ ቡክ አስተያየቶችን እየሰጡ ሲሆን፣ በአንጻሩ የህወሃት ደጋፊ ድረ-ገጾች ለዜናው ትኩረት ሳይሰጡት ቀርተዋል።
ኢህአዴግ ባወጣው መግለጫ የግንባሩ ሊቀመንበር ምርጫ ግልፅ፣ ዴሞክራሲያዊና በትግል ላይ በተመሰረተ ሁኔታ፣ የምክር ቤቱ አባላት በሚስጥር ድምፅ በሰጡበት አካሄድ ተፈጽሟል ብሎአል። “ህዝብን ማዳን፤ሀገርን ማዳንና የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመርን ቀጣይነት ማረጋገጥ ማዕከል ያደረገ በሳል ውይይት መደረጉንና በሳል ውሳኔና ድምዳሜ “ ላይ መደረሱን ገልጿል። “ምርጫውም ኢህአዴግ ያሸነፈበት ምርጫ ነው” በማለትም ኢህአዴግ ለራሱ የአሸናፊነት ምስክርነት ሰጥቷል።
በተቃውሞ ፖለቲካው ጎራ ያሉት አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችም በጉዳዩ ዙሪያ ለኢሳት የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ ዳንኤል ሽበሺ፣ “አብይ ከሚናገራቸው ነገሮች ስንነሳ ለአገር የሚያስብ ጥሩ ሰው እንደሆነ ይሰማኛል። ነገር ግን የዚህ አገር ችግር አብይ ወይም ኃይለማርያም አይደለም፤ የዚህ አገር ችግር ስርዓቱ ነው፤ ህወሃት/ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት ነው፤ የአብይ ወደ ስልጣን መምጣት ብዙ ለውጥ ሲያመጣ አይታይኝም። በኦህዴድ በኩል ጥሩ ሰዎች እንዳሉ ብናይም ህወሃት እያለ ምን ጥሩ ነገር ለሚጣ ይችላል?” በማለት አስተያየቱን በጥያቄ ደምድሟል።
የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት ምክትል ሊ/መንበር መ/ር አለማየሁ መኮንን በበኩላቸው፣ ዶ/ር አብይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስነስቶ ሁሉንም ያካተተ ብሄራዊ እርቅ ይጠራል ብለን እንጠብቃለን ብለዋል። ይህ ሆኖ ካልተገኘ የሚፈጠረው አደጋ የተለዬ እንደማይሆንና ትግሉ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ አብይ ከህወሃቱ ዶ/ር ደብረጺዮን፣ ከደኢህዴኑ ሽፈራው ሽጉጤና ከብአዴኑ ደመቀ መኮንን በተሻለ ከተቃዋሚዎች ጋር መነጋገር መጀመራቸውን ነግረውናል ብለዋል።
የሰማያዊ ፓርቲ የቦረና ዞን ተጠሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው በቀለ በኩላቸው ባለፉት 3 ወራት ኢትዮጵያ አደጋ ውስጥ ትወድቃለች ብለው በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደነበሩ በማውሳት፣ የዶ/ር አብይ መመረጥ ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ እንደማትፈርስ የሚያረጋገጥ ነው ብለዋል። ዶ/ር አብይና አቶ ለማ ከኢህአዴግ አላማ ወጥተው ኢትዮጵያዊነትን ሲያንጸባርቁ ነበር ያሉት አቶ ጌታቸው፣ በውጭ ያሉ ተቃዋሚዎች ሳይቀር ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ በቴሌቪዥን የተናገሩትን ወደ ተግባር ይለውጡታል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
የኦፌኮ ም/ል ሊ/መንበር አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው ፣ የኢትዮጵያን እጣ ፋንታ የሚወስነው ወታደራዊና ደህንነቱ ለጠ/ሚኒስትሩ ምን ያህል ይታዘዙላቸዋል፣ ለህገ መንግስቱንስ ምን ያህል ታማኝ ይሆናሉ፣ በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ነው የሚል አስተያየት ለቢቢሲ ሰጥተዋል።
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) በበኩሉ፣ ዶ/ር አብይ አገሪቱ በብዙ ችግሮች ተተብትባ በተያዘችበት ወቅት መመረጣቸውን ገልጾ፣ የኢትዮጵያ ችግር በገዢው ፓርቲ ብቻ መፍትሄ እንደማያገኝ ማወቅ ይገባል ብሎአል። ለአዲሱ ጠ/ሚኒስትር መልካም የስራ ዘመን የተመኘው ኦዴግ፣ በገዢው ፓርቲ በኩል የመጣው ለውጥ ባለፉት 3 ዓመታት በተደረገው ህዝባዊ ለውጥ የተነሳ መሆኑን ገልጿል።