አብዲ ኢሌን የሚቃወሙ የዲያስፖራ አባላት የታሰሩ ወላጆቻቸውን ለማስለቀቅ ሲባል በኢንተርኔት ይቅርታ እንዲጠይቁ እየተገደዱ ነው

አብዲ ኢሌን የሚቃወሙ የዲያስፖራ አባላት የታሰሩ ወላጆቻቸውን ለማስለቀቅ ሲባል በኢንተርኔት ይቅርታ እንዲጠይቁ እየተገደዱ ነው
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ/ም) በውጭ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ሶማሊያውን የክልሉ ፕሬዚዳንትና ግብረ አበሮቻቸው የሚፈጽሙትን የጅምላ ጭፍጨፋ በመቃወም ድምጻቸውን ማሰማታቸው፣ እንዲሁም የክልሉ ህዝብ ለነጻነቱ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወገኖቹ ጋር በመሆን ለመብቱ እንዲነሳ ዱል ሚድድ የሚል ንቅናቄ መስርተው መታገል መጀመራቸውን ተከትሎ፣ የክልሉ ባለስልጣናት እርሳቸውን የሚቃወሙዋቸውን ሰዎች ወላጆችና ዘመዶች በማሰርና ንብረቶቻቸውን በመዝረፍ ይቅርታ እንዲጠይቁ እያስገደዱ ሲሆን፣ አንዳንዶች ወላጆቻቸውን ለማዳን ሲሉ በአደባባይ ይቅርታ ሲጠይቁ ሌሎች ግን አሻፈረኝ ብለዋል።
ከዱል ሚድድ መስራቾች አንዱ የሆነው ሙሃመድ ሸይክ ቀደም ብሎ የአብዲ ኢሌን አገዛዝ በመቃወም በአንድ ስብሰባ ላይ ድምጹን አሰምቶ ነበር። ሙሃመድ “ የእኛ ጂድዋቅ ጎሳ መሪዎች የሆኑት ጋራድ ኩልምዬ ሞሃመድ ሂርሲ እና ሱልጣን አብዲራህማን ባዴ ጠመንጃ ተደግኖባቸው ከባህላችን ባፈነገጠ ሁኔታ የራሳቸውን ጎሳ አባላት እንዲሳደቡ ተደርጓል። በዚህ ጉዳይ ዝም ማለት አንችልም። ይህ አዲስና አስቀያሚ ነገር ነው። የጅድዋቅ ጎሳ ወንድሞችና እህቶች ነጻነታችን በእጃችን ነው። ለነጻነታችን መሞት አለብን። ለነጻነታችን መቆም አለብን፣ ነጻነት እስከሚመጣም መታገል አለብን።” ብሎ ተናግሮ ነበር ።
በዚህ ንግግር የተበሳጨው አብዲ ኢሌ በቅርቡ የ100 አመት እድሜ ያላቸው እናቱን አስሮ ልጃቸው ሙሃመድ ይቅርታ ካልጠየቀና አብዲ ኤልን እንደሚወድ ካልገለጸ፣ እናቱ እንደሚረሸኑበት ተነገረው። ሙሃመድም በጭንቀት እናቱን ለማዳን ሲል፣ “ ከዛሬ ጀምሮ የፕሬዚዳንት አብዲ ደጋፊ እና በእሱ ከሚያምኑት ሰዎች መሃል አንዱ ሆኛለሁ። ድሮም የመንግስት ደጋፊ ነበርኩ፣ አሁንም ደጋፊ ነኝ። በፊት ላጠፋሁት ጥፋት አላህ ይቅር ይበለኝ። እናትና አባቴ ሆይ በእኔ ምክንያት ከእንግዲህ ችግር አይመጣባችሁም። እወዳችሁዋለሁ። እንደዚሁም ደግሞ በእኔ ምክንያት በእኔ ጎሳ ላይ ችግር አይመጣባችሁም።” የሚል መልእክት ጽፎ በፌስ ቡክ እና በኢንተርኔት ለቀቀ።
ሙሃመድ ይህን ከተናገረ በሁዋላ ወላጆቹ መፈታታቸው ታውቋል።
ሌላው የዱል ሚድድ ንቅናቄ አዘጋጅ የሆነው እና መላው ቤተሰቡ የታሰሩበት በጀርመን ነዋሪ የሆነው አብዱልካስም አብዱላሂ ነው። ቤተሰቡ መታሰራቸው ብቻ ሳይሆን ቤታቸውም ተወርሶባቸዋል። እናቱ ወ/ሮ ሃይባ አርቲ ታፍነው ከተወሰዱ በሁዋላ በልዩ ፖሊስ አዛዡ በጄ/ል አብዱልራሂም ላባ ጎሌ የተላኩ እና በእርሻ ቢሮ ምክትል ሃላፊው አህመድ ሹክሪ እና አሰቃቂ ድርጊቶችን እየፈጸመ ያለው የጄ/ል ላባ ጎሌ ጉዳይ ፈጻሚ አህመድናስር ሃብራዊ፣ በአብዱል ካሲም እናት ላይ አሰቃቂ ድብደባዎችን ሲፈጽሙባት፣ አብዱልካሲም በስልክ እንዲሰማ አድርገውታል።
አብዱልካስም በእናቱ ላይ የሚደርስበትን ስቃይ መቋቋም ስላልቻለ ምንድን ነው የምትፈልጉት ብሎ መጠየቁንና አብዲ ኢሌን እንደሚደግፍ ፌስቡክ ላይ ጽፎ እንዲለጥፍ እንዲሁም በስዊድን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ያዘጋጀውን ስብሰባ እንዲሳተፍ እንደተነገረው ለኢሳት ተናግሯል። አብዱልካሲም ይህን ከተናገረ በሁዋላ እናቱ ከእስር የተለቀቁ ሲሆን፣ ከእስር ከዚህ በሁዋላ አብዲ ኢሌን ተችቶ ቢጽፍ የጎሳው አባላት በሙሉ እንደሚታሰሩ ተነግሮታል።
ሌላው የዱል ሚድድ ንቅናቄ አዘጋጅ የሆነው አብዱልፋታህ ሙሃመድ አባት የሆኑት አቶ ሙሃመድ አህመድ አጋየሬም እንዲሁ ባለፈው ሳምንት ታስረዋል። አቶ ሙሃመድ በከፍተኛ ህመም እየተሰቃዩ ቢሆንም፣ ልጃቸው አብዲ ኢሌን ይቅርታ ካልጠየቀ ህክምና እንደማያገኙና ከእስርም እንደማይፈቱ ተነግሯቸዋል። አብዱልፋታህ ግን ይህን እንደማይቀበል መግለጹን ለኢሳት ተናግሯል።
በመጪው ኤፕሪል 7፣ 2018 አብዲ ኢሌ ከኢትዮጵያ ኢምባሲ ጋር በመተባባር በስዊድን በሚደረገው ስብሰባ ላይ የአብዲ ኢሌ ቀኝ እጅ የሆነውና የስዊድን ጋዜጠኞችን ጆሃን ፐርሹንና ማርቲን ሹብዬን ጨምሮ በርካታ ዜጎችን በመግደልና ሰቆቃ በመፈጸም የሚታወቀው ኒሞ ራረን በስብሰባው ላይ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
አብዲ ኢሌ በተመሳሳይ ቀን የተጠራውን የዱል ሚድድ ስብሰባ እንዳይሰካ ለማድረግ፣ ከኢምባሲው ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ስብሰባ ሲሆን፣ ስብሰባው እንዳይሰካ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መድቦ እየተንቀሳቀሰ ነው። የዱል ሚድድን ስብሰባ ስብሰባ የሚያዘጋጁት የ “ነፍጠኞች” ወኪል ተደርገው እንደሚታዩና በዚህም የተነሳ ውግዘት እንደሚደርስባቸው ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያዊነታቸው እንደማይደራደሩ የሚገልጹት እነዚህ ዜጎች፣ አብዲ ኢሌ የሰበሰባቸው አማካሪዎች ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ያላቸውና በአንድ ወቅት የሲያድባሬ ባለስልጣናት ሆነው ሲሰሩ የነበሩ ናቸው በማለት ለምን ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ለኢሳት አስረድተዋል።
በስዊድን የሚገኙ የክልሉን ተወላጆች እንቅስቃሴ የሚከታተሉት የአብዲሌ ወኪሎች ሃይ ሙሃመድ እና አዳኒ ሙሃመድ ሃሰን የሚባሉ መሆናቸውን ምንጮች አክለው ይገልጻሉ።
በአሁኑ ሰዓት በርካታ ዜጎች በክልሉ ውስጥ ታስረው ይገኛሉ። አብዲ ኢሌ በሶማሊ ክልል ይኖሩ የነበሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያንን ማፈናቀሉ ይታወቃል።