የፖለቲካ ድርጅት ለማቋቋም አስባችኋል የተባሉ 19 ሰዎች ታሰሩ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 17/2010) በአማራ ክልል የፖለቲካ ድርጅት ለማቋቋም አስባችኋል የተባሉ 19 ሰዎች በባህርዳር ከተማ በጅምላ መታሰራቸው ተነገረ።

እስሩ የተፈጸመባቸው ምሁራንና ጋዜጠኞች በብሔር ላይ የተመሰረተ የአማራ ድርጅት በህጋዊ መንገድ ለማቋቁም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው ተብሏል።

በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ የአገዛዙ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ከምርጫ ቦርድ እውቅና አግኝተው የአማራ ብሔራዊ ድርጅት ለማቋቋም እንቅስቃሴ የጀመሩት 19 ሰዎች በወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያው ኮማንድ ፖስት ተለቅመው ታስረዋል።

ከነዚሁም መካከል ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ መምህር፣ አቶ ዮሴፍ ኢብራሒምየወሎ ዩኒቨርስቲ መምህር፣ አቶ በለጠ ሞላ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፈሰር፣ አቶ ካሱ ሃይሉ የእንጅባራ ዩኒቨርስቲ መምህር፣ አቶ አዲሱ መለስ የደብረታቦር ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪም ይገኙበታል።

ከነዚሁ ምሁራን ሌላ የአማራ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ንጋቱ አስረስና ጋዜጠኛ በለጠ ካሳም መታሰራቸው ነው የተነገረው።

በ19ኙም ታሳሪዎች ላይ ድብደባ እንደተፈጸመባቸውም መረጃዎች አመልክተዋል።

የአማራ ድርጅት ለማቋቋም አስባችኋል በሚል በባህርዳር ከተማ የታሰሩት 19ኙ ምሁራንና ጋዜጠኞች እንዲሁም ግለሰቦች አገዛዙ በሚያውቀው ሁኔታ ፓርቲ ለማቋቋም እየተንቀሳቀሱ የነበረ ቢሆንም ለምን በጅምላ ሰብስቦ እንዳሰራቸው የታወቀ ነገር የለም።

ታሳሪዎቹ የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ነው የተነገረው።

አገዛዙ የዲሞክራሲና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ቆርጫለሁ እያለ በተደጋጋሚ መግለጫ ሲያወጣ እንደነበር ይታወሳል።