በቅርቡ ከእስር የተፈቱት ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ታሰሩ በባህርዳር በህቡዕ ልትደራጁ አስባችሁዋል ተብለው የተያዙትም አልተለቀቁም

በቅርቡ ከእስር የተፈቱት ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ታሰሩ
በባህርዳር በህቡዕ ልትደራጁ አስባችሁዋል ተብለው የተያዙትም አልተለቀቁም
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ/ም) በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ፣ በህዝባዊ ጫና ከእስር የተፈቱት ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ወታደራዊ እዙን ሳታስፈቅዱ ስብሰባ አድርጋችሁዋል እንዲሁም አርማ የሌለውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ተጠቅማችሁዋል በሚል ተይዘው ታስረዋል።
ትናንት እሁድ ጆሞ በሚባለው አካባቢ በቅርቡ ከእስር ለተፈቱት ሰዎች በተዘጋጀ የምስጋና ዝግጅት ላይ በመገኘታቸው የታሰሩት አቶ አንዱአለም አራጌ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ጋዜጠኛ በፈቃዱ ሃይሉ፣ ጸሃፊ ዘላላም ወርቃገኘሁ፣ይድነቃቸው አዲስ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አዲሱ ጌታነህ፣ ተፈራ ተስፋዬ፣ ማህሌት ፋንታሁንና ወይንሸት ሞላ ናቸው።
እስረኞቹ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ታስረው ይገኛሉ። በሁሉም እስረኞች ላይ ክስ ይመስረት አይመስረት የታወቀ ነገር የለም።
እንዲሁም በባህርዳር ለወታደራዊ እዙ ሳያሳውቁ ስብሰባ አድርገዋል የተባሉ ከ19 ያላነሱ ምሁራን ፣ ጋዜጠኞችና የህግ ባለሙያዎች ተይዘው ታስረዋል። እነዚህ ወጣቶች በክልሉ የደህንነት ቢሮና በክልሉ ጸጥታ ዘርፍ መያዛቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። እስረኞቹ አዋጁን በመተላለፍ ለወታደራዊ እዙ ሳያሳውቁ ስብሰባ አድርገዋል በሚል በ9ኛ ፖሊስ ጣቢያ እየተመረመሩ ሲሆን፣ በየአካባቢያችሁ ያዘጋጃችሁትን ህዋስ ተናገሩ እየተባሉ ምርምራ እየተደረገባቸው ነው።
ከታሰሩት መካከል በባህርዳር ዩኒቨርስቲ መምህርና የጣና ደህንነትና የአካባቢ ጥበቃ ማህበር ፕሬዚዳንትና ተመራማሪ፣ አቶ ጋሻው መርሻ፣ የሱፍ ሲብራሂም፣ ተመስገን ተሰማ፣ በለጠ ሞላ፣ የአማራ ክልል ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ንጋቱ አስረስ፣ ጋዜጠኛ በለጠ ካሴ፣ ኢንጂነር ሲሳይ አልታሰብ ይገኙበታል። አብዛኞቹ እስረኞች በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በማስተማር ላይ የሚገኙ ናቸው።