የሸካ ጥቅጥቅ ደን በእሳት ቃጠሎ እየወደመ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 14/2010) በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የባህልና የሳይንስ ተቋም ዩኔስኮ የተመዘገበው የሸካ ጥቅጥቅ ደን በእሳት ቃጠሎ እየወደመ መሆኑ ተገለጸ።

እስካሁን 250 ሄክታር የሚሆነው የደኑ ይዞታ በእሳት የወደመ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የአገዛዙ የመገናኛ ብዙሃን ደኑ በሰደድ እሳት መያያዙን ቢገልጹም የተፈጥሮ ሀብት ባለሙያዎች ግን የአካባቢው የአየር ንብረት ሰደድ እሳትን የሚፈጥር አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ።

የአከባቢው ህዝብ እሳቱን ለማጥፋት የሚችል ባለመሆኑ መንግስት በአስቸኳይ ደኑን ከጥፋት እንዲከላከል ጥሪ ተደርጓል።

ኢትዮጵያ የቀራት የደን ይዞታ በምዕራቡ አቅጣጫ የተዘረጋው ሰፊ ጥብቅ ደን ነው።

140ሺህ 377 ሄክታር ስፋት ያለው ሲሆን የሸካ ዞንን ስፋት ግማሽ ያህል የሸፈነ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

በእንስሳት እና እፅዋት ዝርያዎች የበለፀገ እንደሆነም ይነገርለታል።

የምስራቃዊ እርጥበታማ የተፈጥሮ ደን ክምችት ተደርጎ የሚወሰድ፣ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የአየር ንብረት ሚዛን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የሚነገርለት ጥብቅ የደን ይዞታ ነው።

በሀገር በቀል እጽዋት፣ ለህክምና ምርምር የሚወሉ የተለያዩ ተክሎች በርካታ የዛፍ አይነቶች የበቀሉበት ሰፊ የእርሻ መሬት ያለው የገጠር መንደሮች የሚገኙበት ነው።

ከ300 በላይ የተለያዩ ትላልቅ የዛፍ ዝርያዎች፣ 50 አጥቢ እንስሳት፣ 200 የአእዋፍ ዝርያዎችና 20 ተሳቢ ዝርያዎች ያሉት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ቢያንስ 55 እፅዋት እና 10 አእዋፍ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው።

ይህ የኢትዮጵያ ሳምባ በመባል የሚታወቀው ጥብቅ የደን ይዞታ ካለፈው ሳምንት ዓርብ ጀምሮ በእሳት እየወደመ ነው።

በእስከአሁንም ከ20 ሄክታር በላይ የደኑ ይዞታ በእሳት መውደሙ ታውቋል።

ከሳምንት የዘለቀው ቃጠሎ እየሰፋ በመምጣቱ ትልቅ ጥፋት እያስከተለ መሆኑን ከአካባቢው ህዝብ እየቀረበ ካለው የድረሱልን መልዕክት ለመረዳት ተችሏል።

የሸካ ዞን ባለስልጣናት ህዝቡ እየተረባረበ ቢሆንም በህዝብ አቅም የሚጠፋ አልሆነም።

የፌደራል መንግስት በአስቸኳይ ምላሽ ይስጥ በማለት ጥሪ አድርገዋል።

በአገዛዙ መገናኛ ብዙሃን በኩል እየቀረበ ያለው የቃጠሎ መንስዔ ሰደድ እሳት ቢሆንም የአካባቢው ተወላጅና የተፈጥሮ ሀብት ባለሙያ አቶ አየለ አንገሎ ግን ሰደድ እሳት የሚለው ምክንያት የሚያሳምናቸው አልሆነውም።

የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግስት እስከአሁን የወሰዱት ርምጃ አለመኖሩም ተገልጿል።

የሸካ ህዝብ እየተረባረበ ቢሆንም የእሳቱን መስፋፋት ሊያቆመው አልቻለም።

ለአንድ ሳምንት ያህል በውሃና አፈር ብቻ የእሳቱን ግስጋሴ ለመግታት እየሞከረ ያለው የሸካ ህዝብ የድረሱልን ጥሪ እያቀረበ ነው።