(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 13/2010) በግማሽ አመት የተገኘው የወጪ ንግድ ገቢ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በታች መሆኑ ተገለጸ።
ምርት በመላክ የውጭ ምንዛሪ ከተገኘባቸው የአለማችን ሃገራት መካከል ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባችው ሶማሊያ በሁለተኛ ደረጃ ተመዝግባለች።
የመጀመሪያ ግማሽ አመት ሪፖርቱን ያመጣው የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ከወጪ ንግድ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ 1 ነጥብ 35 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር መሆኑን ይፋ አድርጓል።
በሌላ በኩል በተጠቀሰው የበጀት ዘመን ወደ ሀገር ውስጥ የገባው ምርት ከ8 ቢሊየን ዶላር በላይ በመሆኑ የንግድ ሚዛን ጉድለቱ ከ6 ቢሊየን ዶላር በላይ ማሻቀቡን መረጃዎች አመላክተዋል።
ይህም ሃገሪቱን በከፍተኛ ሁኔታ የሸቀጥ ማራገፊያ ያደረገ ሲሆን የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በኢኮኖሚው ላይ አደጋ መጋረጡ ተገልጿል።
ለስራአቱ ቅርበት ያላቸው የፕሬስ ውጤቶች እንደገለጹት በአሁኑ ሰአት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ረሃብ ተከስቷል።
ከምንም ነገር በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ባለመቻሉና የውጭ ምንዛሪ ይዘው የሚመጡ ባለሃብቶች ባለመኖራቸው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ እየተዳከመ የበለጠ ቀውስ የሚፈጠርበት ሁኔታ ታይቷል።
ኢኮኖሚው ላይ የተፈጠረው ችግር ከፖለቲካው ያልተናነሰ ቀውስ ሊያመጣ እንደሚችል የፕሬስ ውጤቶቹ አስጠንቅቀዋል።
በሌላ በኩል ምርት በመላክ የውጭ ምንዛሪ ከተገኘባቸው የአለማችን ሃገራት መካከል መረጋጋት የተሳናት ሶማሊያ ከቻይና ቀጥላና ከአሜሪካ ልቃ በሁለተኛ ደረጃ ተመዝግባለች።
ይህም የንግድ ሂደቱ ጤናማነቱና ዘላቂነቱ ላይ ጥያቄ እንደሚያስነሳ ኢሳት ያናገራቸው የዘርፉ ሙያተኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የሶማሊያ መንግስት በበርበራ ወደብ ምክንያት “የኢትዮጵያ መንግስት አለም አቀፍ ህግን ከመጻረሩም በላይ ሉአላዊነቴን ደፍሯል” ማለቱ የሚታወስ ነው።