(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 13/2010)ወደ አውሮፓ ሳይሻገሩ ባህር ላይ የሰመጡ ስደተኞች ቁጥር ባለፈው ዓመት ብቻ ከ5ሺህ በላይ እንደነበር ተዘገበ።
ከወራት በፊት አንድ የጀርመን ጋዜጣ ባውጣው ዘገባ ከ33ሺህ የሚበልጡ ሟቾችን ዝርዝር ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
ዴር ታግ ኢስፒግል የተባለው የጀርመን ጋዜጣ በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው መረጃ ከሆነ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1993 ወዲህ ባለው ጊዜ ብቻ 33ሺ 293 ስደተኞች ወደ አውሮፓ ሊሻገሩ ሲሉ ባህር ውስጥ ሰምጠው ሞተዋል።
ከነዚሁም መካከል በሜድትሪንያን ባህር በኩል የሞቱት ስደተኞች ቁጥር እጅግ የበዛ መሆኑን ጋዜጣው ጠቅሷል።
በአውሮፓ ስደተኞችን የመገደብ ፖሊሲ ሳቢያ ከተለያዩ ሃገራት ባህር ለመሻገር ሲሞክሩ ከሞቱት መካከል ሕጻናትና ታዳጊዎች እንደሚገኙበትም በጋዜጣው ተመልክቷል።
ባህር ሊሻገሩ ሲሉ የሞቱትን ከ33ሺ በላይ ስደተኞችን ስም ዝርዝር በ46 ገጽ ወረቀት ላይ ያሰፈረው የጀርመኑ ጋዜጣ ለደረሰው ጥፋት የአውሮፓ ሃገራትን ተችቷል።
እንደ ጋዜጣው ዘገባ ባለፈው አመት ብቻ የሜድትራኒያን ባህርን ተሻግረው ለመግባት የሞከሩት 5 ሺ 79 ስደተኞች በቅዝቃዜና በመስመጥ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በከፍተኛ ቁጥር ከሞቱት ስደተኞች መካከልም አፍሪካውያን ትልቁን ድርሻ ሲይዙ የኛዎቹ ኢትዮጵያውያንም የዚሁ ስደትና የባህር ላይ ሞት ሰለባ መሆናቸውም በተደጋጋሚ ሲነገር መቆየቱ አይዘነጋም።