የዋልድባ መነኮሳት ለአንድ አመት ያህል በአንድ ልብስ ብቻ መቆየታቸውን ገለጹ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 30/2010) በእስር ላይ የሚገኙት የዋልድባ መነኮሳት ለአንድ አመት ያህል በአንድ ልብስ ብቻ በጨለማ ቤት መቆየታቸውን ለፍርድ ቤት ገለጹ።

በተለይም በአባ ገብረስላሴና በአባ ገብረየሱስ ላይ የተፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት አስከፊ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ የማረሚያ ቤቱን መልስ ከተቀበለ በኋላ ሁኔታውን መርምሮ መልስ እንደሚሰጥ ገልጿል።

እስረኞቹን ለመጠየቅ የመጡ ሰዎች ለመነኮሳቱ ልብስ እንዲሰጡም ፍርድቤቱ መፍቀዱ ታውቋል።

የዋልድባ መነኮሳት ክሳቸው እንደተቋረጠ በሪፖርትር ጋዜጣ መገለጹ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ የመነኮሳቱ የክስ ሂደት ዛሬም በፍርድ ቤት መቀጠሉ ነው የተነገረው።

ዛሬ የካቲት 30 በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ ታዲያ የዋልድባ መነኮሳት በእስር ቤቱ የደረሰባቸውን እንግልትና ስቃይ ለዳኞች አስረድተዋል።

መነኮሳቱ ለአንድ አመት ያህል ልብስ እንዳይቀይሩ ከመደረጋቸውም ሌላ በጨለማ ቤት ውስጥ ተለያይተው እንዲቀመጡ መደረጉንም ነው ለችሎቱ የገለጹት።

በተለይም አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነማርያም ዞን አምስት ተብሎ በሚጠራው እስር ቤት በጨለማ ቤት ውስጥ የደረሰባቸውን ስቃይ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።

አባ ገብረስላሴ ለአንድ አመት ያህል ልብስ ሳይቀይሩ በጨለማ እስር ቤት መቆየታቸውም ለፍርድ ቤቱ ቀርቧል።

ፍርድቤቱም ይህ ለምን እንደሆነ ጠይቆ ከእስር ቤቱ በደብዳቤ ምላሽ በማግኘቱ ሁኔታውን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለመጋቢት 5/2010 ቀጠሮ ሰቷል።

ዳኞቹ ለመነኮሳቱ ለምን ልብስ እንዳይገባ ተደረገ ሲሉ በጠየቁ ጊዜ ችሎቱን ሲከታተሉ ከነበሩ ጠያቂዎች አንዱ ልብስ ይዞ በመገኘቱ ዳኞቹ እንዲሰጣቸው አድርገዋል ነው የተባለው።

የእስር ቤቱ ሃላፊ ልብስ እንዳይሰጣቸው ቢከለክሉም ዳኞቹ በቁጣ ልብስ እንዲሰጥ ማድረጋቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የዋልድባ መነኮሳቱ መደበኛ ክስ መጋቢት 18 እንደሚቀጥልና ምስክሮችን የመስማት ሒደት እንደሚኖርም ተገልጿል።