ወደ ውጭ የሚላከው እቃ በመጥፋቱ አብዛኛው የአየር መንገዱ የጭነት አገልግሎቱ ተቋርጧል ተባለ

ወደ ውጭ የሚላከው እቃ በመጥፋቱ አብዛኛው የአየር መንገዱ የጭነት አገልግሎቱ ተቋርጧል ተባለ
(ኢሳት ዜና የካቲት 29 ቀን 2010 ዓ/ም) በኦሮምያ የሚካሄደውን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ ከክልሉ የሚመጡና ወደ ውጭ አገር በኢክስፖርት ስም የሚላኩ እቃዎች በመቋረጣቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ አገልግሎት በአብዛኛው ስራ ማቋረጡን ምንጮች ገልጸዋል።
አመጹ ከመጀመሩ በፊት እረፍት ያልነበረው የአየር መንገዱ የጭነት አገልግሎት ፣ በአሁኑ ሰአት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አገልግሎት እየሰጠ ባለመሆኑ በአየር መንገዱ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ይናገራሉ።
በጭነት (ካርጎ) አግልገሎት ላይ የሚሰሩ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ፣ ብዙዎቹ እረፍት እንዲወስዱ መደረጉን ምንጮች ገልጸው፣ የስራ ማቆም አድማው የሚቀጥል ከሆነ በአየር መንገዱ ህልውና ላይ ቀላል የማይባል ተጽኖ ይፈጥራል ብለዋል።
በተከታታይ የተደረጉት የስራ ማቆም አድማዎች በቡና፣ በጫት፣ በተለያዩ ማዕድናት የንግድ እንቅስቃሴ እንዲሁም በቱሪዝም ላይ ከፍተኛ ተጽኖ ያሳደሩ ሲሆን፣ በአገሪቱ ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረትም እንዳባባሱት የሚደርሱን መረጃዎች ያሳያሉ።