የጎሳ ግጭቶችን ተከትሎ በኢትዮጵያ አዲስ የርሃብ አደጋ እያንዣበበ መሆኑን ዓለም አቀፍ የቤተክርስቲያናት ህብረት አስታወቀ
(ኢሳት ዜና የካቲት 29 ቀን 2010 ዓ/ም) በአሁኑ ወቅት ያለው የድርቅ ሁኔታ ካለፈው ዓመት 2017 እ.ኤ.አ. ጋር ሲነጻጸር በከፋ ደረጃ ላይ ይገኛል የሚለው ህብረቱ፣ በተለይም በአፋር፣ በሶማሊያና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ አርብቶ አደሮች በድርቁ ክፉኛ ተጠቅተዋል ።
በኢትዮጵያ ካለፉት አርባ ዓመታት ጀምሮ በተደጋጋሚ ጊዜያት ረሃብ እየተከሰቱ ነው። በአገሪቱ የርሃብ አደጋዎች ከዓመት ወደ ዓመት ከመደጋገማቸው በተጨማሪ እየከፋም መጣቱንም ኅብረቱ አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት የተከሰተው ረሃብ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በዘውግ ላይ ካነጣጠሩ የፖለቲካ ግጭቶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው። በተለይም ሰፊውን የድንበር ወሰን በሚዋሰኑት የሶማሊያና የኦሮሞ አካባቢዎች የሚታየው ግጭት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ ኅብረቱ በሪፖርቱ አመላክቷል።
ገዥው ፓርቲ አስቸኳይ የጊዜ አዋጅ ቢያውጅም መጠነ ሰፊ በሆነ ሁኔታ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው አሁንም መፈናቀላቸውን ቀጥለዋል። በመላ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቀት ያሉት ግጭቶች እጅግ ወደ ከፋ ደረጃ ተቀይሮ ረሃብ እንዲፈጠር አድርገዋል። ግጭትና ረሃብ በመሸሽ ከቀያቸው የፈለሱ ሰላማዊ ዜጎች መጠለያ ጣቢያዎችን እየቀያየሩ አሳሳቢ በሆነ ይዞታ ላይ ይገኛሉ።
የዓለም አቀፍ የቤተክርስቲያናት ህብረት ቁጥራቸው ከ250 ሽህ በላይ ለሚሆኑ ፍልሰተኞች አፋጣኝ የሆነ ድንገተኛ እርዳታ በመስጠት እንቅስቃሴ መጀመሩን ሪሊፍ ዌብ ዘግቧል።