በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 28 አገራዊና ክልላዊ ፓርቲዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲሰረዝ ጠየቁ።
(ኢሳት ዜና የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ/ም) ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ተፈጥሮ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረትም ጠይቀዋል።
ፓርቲዎቹ ባወጡዋቸው 5 የአቋም መግለጫዎች፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲሰረዝ፣ የዜጎች መፈናቀል በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እውን እንዲሆንና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲከፈት፣ ብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ እንዲደረግና ከመቀባበር ፖለቲካ ወደ ሰለጠነ ህገመንግስታዊ የሽግግር ስርዓት ሽግግር እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ፓርቲዎቹ መግለጫውን ያዘጋጁት ምርጫ ቦርድ ለፓርቲ አመራሮች በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው የግጭት አፈታት ስልጠና ላይ በመሳተፍ ላይ እያሉ ነው።
የፖለቲካ ድርጅቶች መግለጫውን ሲያዘጋጁ የኢህአዴግ እና የኦህዴድ ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን፣ ሁለቱም በመግለጫው ላይ ተቃውሞ አላሰሙም። ይሁንና በመግለጫው ላይ ግን ፊርማቸውን አላኖሩም።
መግለጫውን ካወጡት መካከል በርካታዎቹ ከገዥው ፓርቲ ጋር በድርድር ላይ ያሉ ናቸው።