በአሲድ ጥቃት ቃጠሎ የደረሰባትን ኢትዮጵያዊት ለመርዳት እርዳታ እየተሰበሰ ነው

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 28/2010) በአሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት በአሲድ ጥቃት ቃጠሎ የደረሰባትን ኢትዮጵያዊት ለመርዳት የእርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ተጀመረ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባልደረባ የነበረችውና አሜሪካ ከገባች ገና ሁለት አመት ብቻ ያስቆጠረችው ኢትዮጵያዊት የአሲድ ጥቃት የተፈጸመባት በደባልነት በሚኖር ግለሰብ እንደሆነም ኒውስ ፎር ቴሌቪዥን በዘገባው አመልክቷል።

ሰላማዊት ተፈራ የተባለችውን ኢትዮጵያዊት ከሳምንት በፊት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር የካቲት 24/2018 ከምሽቱ 1 ሰአት ከ30 አካባቢ ሰልፈሪክ አሲድ የደፋባት በክሪ አብደላ የተባለ ግለሰብ ነው።

ግለሰቡ ለጊዜው የተሰወረ ቢሆንም ከሁለት ቀናት በኋላ ግን በቁጥጥር ስር መዋሉ ታውቋል።

ጥፋቱን እንዳመነ የተገለጸው ይህ ግለሰብ የመግደል ሙከራ ክስ እንደሚቀርብበትም ተመልክቷል።

ሰላምዊት ተፈራ ግለሰቡ አሲዱን እንደደፋባት እየጮኽች ከቤት መውጣቷንና የእርዳታ ተማጽኖ ጥሪ ስታሰማ መቆየቷን ጎረቤቶቿ ለዋሽንግተን ዲሲው ኒውስ ፎር ቴሌቪዥን ገልጸዋል።

አሲዱ ልብሷን ጭምር ስላቃጠለው እርቃን በሚባል ደረጃ ስትሮጥ መታየቷንም ከዘገባው መረዳት ተችሏል።

ጥቃቱን ከፈጸመ ከሁለት ቀናት በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው የ28 አመቱ በክሪ አብደላ ወንጀሉን መፈጸሙን ያመነ ቢሆንም ለወንጀሉ የገፋፋው ምክንያት ምን እንደሆነ እየተመረመረ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።

በዚህ ዙሪያ መረጃ ያላቸው ወገኖች በ301-699-2601 ጥቆማ እንዲሰጡ የሜሪላንድ ግዛት የጆርጂያ አውራጃ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።

ሰላማዊት ተፈራ ላይ የደረሰው ቃጠሎ 2ኛና 3ኛ ደረጃ መሆኑም ተገልጿል።

በዋሽንግተን ዲሲ አቅራቢያ ሜሪላንድ ግዛት ሃይትስቪል ነዋሪ ለሆነችው ወጣቷ ኢትዮጵያዊት ሰላማዊት ተፈራን የሕክምና ወጪ ለመሸፈን የሚያስችል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ጎ ፈንድ ላይ ተጀምሯል።

50ሺ የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ትላንት የተጀመረው የገቢ ማሰባሰቢያ በአንድ ቀን ከ10ሺ የአሜሪካን ዶላር በላይ እንደተገኘበት ታውቋል።

ሌሎች ኢትዮጵያውያንም እንዲደግፉ ጥሪ ቀርቧል።