ድጋፍ የሰጡ የምክር ቤት አባላት ከ 2/3ኛ በታች መሆናቸው ታወቀ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 23/2010)

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ለማጽደቅ በተጠራው የፓርላማ ስብሰባ ድጋፍ የሰጡ የምክር ቤት አባላት ከ 2/3ኛ በታች መሆናቸው ታወቀ።

ይህም በህገመንግስቱ መሰረት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ውድቅ መሆኑን ያሳያል ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

ሆኖም የመንግስት እና የፓርቲ መገናኛ በዙሃን የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ጸድቋል ሲሉ ዘግበዋል።

ጸድቋል በሚል ይፋ ያደረጉት ቁጥር ከሚጠበቀው በታች በመሆኑ ከሰዓታት በኋላ ቁጥሩን ለመቀየር ተገደዋል።

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በፓርላማው ተቀባይነት እንዲያገኝ ከምክር ቤት አባላት ቢያንስ 364ቱ እንዲደግፉት የሚጠበቅ ቢሆንም ፣የደገፉት 346 የምክር ቤት አባላት መሆናቸውን የፓርላማው ማህበራዊ ገጽ እንዲሁም የመንግስት እና የፓርቲ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በዕለቱ የነበሩት የምክር ቤት አባላት 441 ሲሆኑ ፣106 አባላት አለመገኘታቸውም ታውቋል።

በዕለቱ ከነበሩት የምክር ቤት አባላት 88ቱ ሲቃወሙ 7ቱ ድምጸ ተአቅቦ ማድረጋቸውም ተዘግቧል።

ይህ በፓርላማው ይፋ የሆነው ቁጥር  የህግ ክፍተት እንዳለበትና አዋጁ ውድቅ  መሆኑን ያረጋግጣል መባሉን ተከትሎ ፓርላማው እንዲሁም የመንግስት እና የፓርቲ መገናኛ ብዙሃን የቁጥር ማስተካካያ አድርገዋል።

346 የፓርላማ አባላት ደገፉት የሚለውን 395 የፓርላማ አባላት ደገፉት ወደሚል ለውጠውታል።

ለግል መገናኛ በዙሃንም የቆጠራ ስህተት ተገኝቶበታል በሚል ዘገባቸውን በ395 እንዲያስተካክሉ መደርጋቸውንም ከሪፖርተር ዘገባ መረዳት ተችሏል።ሪፖርተርም በዚሁ መሰረት ዘገባውን አስተካክሏል።

የፓርቲና የመንግስት እንዲሁም ሃገር ቤት የሚገኙ የግል መገናኛ ብዙሃን ቁጥሩን ከለወጡት በኋላ ፓርላማው ውስጥ አፈጉባኤው በድምጽ ይፋ ያደረጉት ውጤት ከነድምጻቸው በኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ (OMN) በኩል ተሰራጭቷል።

በዚህም አዋጁን የደገፉ የምክር ቤት አባላት 346 ብቻ መሆናቸውም ተረጋግጧል።

ይህም አዋጅ በህግ አይን ተቀባይነት የሌለው ወይንም ውድቅ መደረጉን ያረጋግጣል የሚሉት የሕግ ባለሙያዎች ዓለም አቀፉ ማህረሰብ በጉዳዩ ላይ ድምጹን ያሰማል የሚል ዕምነትም አላቸው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር  ቤት አባላቱ ከብዙ ማስፈራሪያ በኋላ በዚህ መጠን መቃወማቸው እና መቅረታቸው በብዙዎች ዘንድ ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል።