የአድዋ ድል በአል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

የአድዋ ድል በአል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ
(ኢሳት ዜና የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ/ም)122ኛው የአድዋ ድል በአል በአዲስ አበባና በአድዋ ተራሮች ላይ በድምቀት ተከብሯል። በአዲስ አበባ የተለያዩ ወጣቶች በአሉን በተለያዩ የጥበብ ስራዎችን አድምቀውት ውለዋል።
ወጣቶቹ አባቶቻቸው የሰሩት አኩሪ ታሪክ እነሱም ጭቆና በማስወገድ እንደሚደግሙት ሲናገሩ ተሰምተዋል። በቅርቡ ከእስር የተለቀቁ ወጣቶች በስፍራው መገኘታቸውን ተከትሎ በርካታ ፖሊሶች ወጣቱን ለአመጽ ለማነሳሳት እየቀሰቀሳችሁ ነው በሚል አግተዋቸው እንደነበርና በሁዋላ ላይ እንደበተኑዋቸው በስፍራው የነበሩ የአይን እማኞች ገልጸዋል። አብዛኞቹ ወጣቶች በስፍራው ተገኝተው የፖለቲካ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።
በስፍራው የተገኘው ወኪላችን “ ዛሬ ሌላ አገር ውስጥ ያለሁ ነው የመሰለኝ፣ በህዝቡ ውስጥ ፍርሃት የሚባል ነገር የለም። በበአሉ ላይ የተገኙት ሁሉ በወኔ ነበር አገራዊ ይዘት ያላቸውን መዝሙሮች ይዘምሩ የነበረው። ፖሊሶችን ሲያዩ ደግሞ ይብስባቸዋል።” ሲል ትዝብቱን ገልጿል። በበአሉ ላይ የተገኙት አባት አርበኞችም ወጣቱ የአባቶቹንና የእናቶቹን አደራ እንዲያስጠብቅ ምክራቸውን ሲለግሱ ነበር።
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ተደራጅቶ ለወረራ የመጣውን የጣሊያንን ጦር ድባቅ በመምታት ለመጀመሪያ ጊዜ ነጭ ቅኝ ገዢዎችን አሸንፎ ታሪክ የሰሩበት ቀን ነው። ቀኑ በነጭ የአገዛዝ ቀንበር ስር ወድቀው ለነበሩት የጥቁር የሰው ዘሮች በሙሉ የትግል ወኔን የቀሰቀሰ ሲሆን፣ በተለይ በአፍሪካ ለተደረጉት የጸረ ቅኝ ግዛት ትግሎች አድዋ እንደ መነሻና ማነቃቂያ ማገልገሉን የታሪክ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የአድዋን ድል ተከትሎ በርካታ የምዕራባውያን አገራት ለኢትዮጵያ ነጻነት እውቅና ለመስጠት ተገደዋል። በአጼ ሚኒሊክና በባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ በተመራው ጦር ላይ ከአራቱም ማዕዘናት የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን መሰለፋቸው ለተገኘው ድል አስተዋጽኦ ማድረጉን የታሪክ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።