(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 22/2010)
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የሙስና ደረጃ የሚያሳየውን አመታዊ ሪፓርት ይፋ አደረገ።
በሕውሃት/ኢህአዴግ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት በሙስና ከተዘፈቁት ሃገራት አንዱ መሆኑን ሪፓርቱ ገልጿል።
የሚዲያ ነፃነት አለመኖርና መንግስታዊ ያልሆኑ ሲቪክ አደረጃጀቶች አለመጠናከራቸው ሙሰኝነት እንዲባባስ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
መቀመጫውን ጀርመን በርሊን ከተማ ያደረገው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በየአመቱ የሃገራትን የሙስና ደረጃ በማውጣት ይታወቃል።
ይህ ከመቶ በላይ ቅርንጫፎችን በመላው አለም በማቋቋም የአገራትን የሙስና ኢንዴክስ የሚያወጣው ተቋም ሰሞኑን የ2017 ዓመታዊ ሪፓርቱን ይፋ አድርጓል።
ሪፓርቱ እንዳመላከተውም በአለም አቀፍ ደረጃ እየተመዘገበ ያለው የሙስና ሁኔታ እየተባባሰ ሔዷል።
በተለይም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2012 ጀምሮ ባሉት ስድስት አመታት ሃገራት ሙስናን ለመዋጋት ያደረጉት ጥረት አነስተኛ መሆኑን ሪፓርቱ ገልጿል።
በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት መሰረት የፕሬስ ነፃነት እና ጠንካራ መንግስታዊ ያልሆኑ አደረጃጀቶች የሌሉባቸው ሃገራት የሙስና ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነው።
የነፃ ሚዲያ መኖር ከዲሞክራሲ ግንባታ ጋር አዎንታዊ ቁርኝት እንዳለው የገለፀው ይህ ሪፓርት ፣ በአንድ አገር ውስጥ የሙስና መስፋፋትና የሚዲያ ነፃነት መታፈን ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው አውስቷል።
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ለአገራት የሙስና ደረጃ ውጤት የሚሰጠው ከአንድ እስከ መቶ ባለው አሃዝ ሲሆን በከፍተኛ ሙስና የተዘፈቁ ሃገራት ከ50 በታች የሚያገኙት ናቸው።
በዚህ መሰረት በ2017 የሙስና ደረጃ ሪፓርት 89 ከመቶ በማግኘት ከሙስና በመራቅ የአንደኝነት ደረጃውን የያዘችው ኒውዝላንድ ስትሆን በ88 ነጥብ ዴንማርክ ሁለተኛውን ደረጃ ይዛለች።
በአካባቢያዊ ንፅፅር ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት በአማካይ 32 በመቶ በማስመዝገብ ሙስና የተንሰራፋባቸው ምድብ ውስጥ ገብተዋል።
በሕውሃት/ኢህአዴግ የምትመራው ኢትዮጵያ ከመቶ ያገኘችው ውጤት 35 በመቶ በመሆኑ በሙሰኝነት ከተዘፈቁ አገራት አንዷ ሆናለች።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2012 ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት አመታት በኢትዬጵያ ሙሰኝነት በመባባሱ ምክንያት የተመዘገበው ውጤት ከ35 በመቶ በታች ሆኗል።
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው በኢትዮጵያ የሚዲያ ነፃነት መገደቡ፣ ጠንካራ መንግስታዊ ያልሆኑ ማህበራዊ አደረጃጀቶች አለመኖራቸውና የሃገሪቱ ፓለቲካዊ ሁኔታ ባለመረጋጋቱ ምክንያት ሙስና በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቷል።
በሃገሪቱ ገለልተኛ ሚዲያዎች ባለመኖራቸው የመንግስት አሰራር ግልፅ ሆኖ ተጠያቂነት ማምጣት እንዳልቻለም ሪፓርቱ አመላክቷል።