የአገዛዙ ታጣቂዎች አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 20/2010)

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላም ቢሆን ሕዝቡ ተቃውሞውን በመቀጠሉ የአገዛዙ ታጣቂዎች አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ መታዘዙን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ገለጸ።

ኮማንድ ፖስቱ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴና ደምቢዶሎ የተካሄደውን የሕዝብ ተቃውሞ በመጥቀስ የአገዛዙ ታጣቂዎች የሕዝብ ሕይወት እንዳይጠፋ ጥንቃቄ ከማድረግ ይልቅ ርምጃ እንዲወስዱ ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

የፓርላማ አባላት አስቸኳይ ጊዜውን እንዳያጸድቁ በሕዝብ ግፊት እየተደረገባቸው መሆኑም ሕገ ወጥ ተግባር ነው ብሏል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ባለፉት ሁለትና ሶስት ቀናት በኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይም በነቀምቴና ደምቢዶሎ የተፈጠረው ሁኔታ የአፈጻጸም መመሪያውን የጣሰ ነው ብሏል።

በነዚሁ አካባቢዎች የእጅ ቦምቦች ሳይቀር ተወርውረዋል ያለው መግለጫ የመንግስት ታጣቂዎች የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ጥንቃቄ በማድረጋቸው ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል አስታውሷል።ተቃውሞውን ያስነሱት ጸረ ሰላም ሃይሎች ናቸው ሲልም የሕዝቡን ተቃውሞ መግለጫው አጣጥሎታል እናም የአገዛዙ ታጣቂዎች መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ መቸገራቸውን ተረድቻለሁ ነው ያለው።

ስለሆነም ከአሁን ወዲህ ተመሳሳይ ተቃውሞ የሚቀጥል ከሆነ የመንግስት ታጣቂዎች ርምጃ እንዲወስዱ ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል ብሏል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚቆጣጠረው ኮማንድ ፖስት።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የፓርላማ አባላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዳያጸድቁ በስልክ እና በአካል በማግኘት ግፊት እየተደረገባቸው መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ገልጿል።

ይህም ህገወጥ ስለሆነ የፓርላማ አባላትና ቤተሰቦቻቸው ለኮማንድ ፖስቱ በማመልከታቸው ድርጊቱ እንዲቆም ርምጃ ይወሰዳል ነው ያለው።

የካቲት 9/2010 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጸድቆ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ሕዝቡ ተቃውሞውን በመቀጠል ድንጋጌውን መጣሱ አገዛዙን አስቆጥቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተጣሰው ደግሞ በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በባህርዳር፣በጉራጌ ዞን፣በላሊበላና ጎንደርን በመሳሰሉ አካባቢዎችም ጭምር ነው።እናም ሁኔታው እየሰፋ በመምጣቱ ኮማንድ ፖስቱ ርምጃ እንዲወስድ አገዛዙ ተጨማሪ መግለጫ ለማውጣት መገደዱን በመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሰበር ዜና የወጣው መረጃ ያመለክታል።