በነቀምቴ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ አንድ ሰው ሲሞት በርካታ ሰዎች ቆስለዋል
(ኢሳት ዜና የካቲት 20 ቀን 2010 ዓ/ም) ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ በቅርቡ ከእስር የተፈቱት የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ከነቀምቴ ህዝብ ጋር ለመገናኛት ያደረጉት ሙከራ አዋጁ አይፈቅድም በሚል ሰበብ በወታደሮች እንዲገታ ከተደረገ በሁዋላ፣ ህዝቡ ተቃውሞውን ያሰማ ሲሆን፣ ወታደሮች በወሰዱት እርምጃ 1 ሰው መገደሉንና 7 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የኦሮምያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል። ከወታደሮችም መካከል የቆሰሉ መኖራቸውንም አቶ አዲሱ ገልጸዋል።
የነቀምቴ ህዝብ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ፣ ከፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ጋር የመገናኘት መብቱ እንዲከበርለት እና ጥያቄዎቹ መልስ እንዲያገኙ ጥያቄ ሲያቀርብ እንደነበር ተዘግቧል።
ኮማንድ ፖስት በሚል ራሱን የሚጠራው ክፍል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ደግሞ ባለፉት ሁለት እና ሶስት ቀናት በኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይም በነቀምትና ደምቢዶሎ ከተሞች ህገወጥ ሀይሎች በፀጥታ ሀይሎች ላይ የእጅ ቦምብ በመወርወር አደጋ ለማድረስ ሞክረዋል ብለዋል።
ኮማንድ ፖስቱ “እነዚህ ሀይሎች ከዚህ የጥፋት ድርጊታቸው በአፋጣኝ የማይቆጠቡ ከሆነ በአስቸካይ ጊዜ አዋጁ እና በመመሪያው መሰረት በእነዚህ አካላት ላይ አስፈላጊ የተባለውን እርምጃ ሁሉ እንዲወስዱ ለፀጥታ ሀይሎች ትእዛዝ” ሰጥቻለሁ ብሏል።
የአሜሪካን መንግስት ጨምሮ በርካታ መንግስታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እየተቃወሙት ይገኛሉ። አዋጁ ችግሮችን የሚያባብስ እንጅ ችግሩን የሚፈታ ባለመሆኑ አሜሪካ አዋጁን በይፋ ለመቃወም እንደተገደደች በመግለጽ ላይ ናት። የህወሃት/ኢህአዴግ ባለስልጣናት በአሜሪካ አቋም ባለመደሰት ከአሜሪካ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበው፣ አሜሪካ ተገቢውን ማብራሪያ እንደሰጠች ታውቋል።