ከአርባ ምንጭ ከተማ በሽብር ክስ ተከሰው ሰሞኑን የተለቀቁ የከተማዋ ወጣቶች አሁንም በነጻነት መንቀሳቀስ አልቻልንም አሉ
(ኢሳት ዜና የካቲት 20 ቀን 2010 ዓ/ም) ነዋሪነታቸው በአርባምንጭ ከተማ የሆኑት የአንድ ቤተሰብ አባላትን ጨምሮ በተመሳሳይ ክስ ተከሰው በማእከላዊ እስር ቤት፣ በሸዋ ሮቢት፣ በቂሊንጦና ዝዋይ እስር ቤቶች ውስጥ ሰብዓዊ መብታቸው ተጥሶ በእስር ሲንገላቱ የቆዩት ወጣቶች፣ ከእስር ከተፈቱም በሁዋላ እንግልቱ እንዳልቀረላቸው ይናገራሉ።
እጃቸው በተያዘበት ወቅት ”ከመቼ ጀምሮ ነው ደቡቦች ለመብታችሁ መጠየቅ የጀመራችሁት፣ ኃ/ማሪያም ተሹሞ የለም ወይ፣ ምን አግብቶህ ነው ከአማራ ጎን የምትቆመው፣ ምን የጎደለባችሁ ነገር አለ የሚሉ ስነልቦናዊ ጥቃቶችን ጨምሮ፣ የተለያዩ አካላዊ ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው እና ሕክምና እንደተከለከሉ ጉዳተኞቹ ገልጸዋል።
በነጻ ተለቀው ወደ ትውልድ ከተማቸው ሲገቡ በሕዝቡ ደማቅ አቀባበል ቢደረግላቸውም፣ በከተማው አስተዳደርና የጸጥታ አካላት ግን ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሳቸው በመሆኑ የደኅነት ሥጋት ውስጥ መሆናቸውን ጉዳተኞቹ አክለው አስታውቀዋል።
በመኖሪያ ቤታቸው የተዘጋጀላቸው የእንኳን ደህና መጣችሁ ግብዣ ያስቆጣቸው የፖሊስ አባላት ጎብኝዎቹቻቸው በተወሰኑ ሰዓታት እንዲመጡ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣልን ጨምሮ ዛቻና ማስፈራሪያዎች እያደረሱባቸው ነው። ካለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ምሽት ላይ ወደ ቤታቸው በመግባት መኖሪያ ቤታቸው እንዲፈተሽ መደረጉንም ገልጸዋል።
የከተማውን ነዋሪዎችን ስብሰባ በመጥራት “ አሸባሪዎች ቤት ለምን ትሄዳላችሁ፣ የቴዲ አፍሮን ሙዚቃ እየሰማችሁ ለምን ትጨፍራላችሁ፣ የሚሉና ሌሎችንም የአገር አንድነትን የሚሸረሽሩ ንግግሮችን የከተማው የፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ተመስጌን እንደተናገሩ ወጣቶች አጋልጠዋል። ተወልደው ባደጉበት ከተማ ውስጥም የቀበሌ መታወቂያ ካርድ እንዳያገኙ መከልከላቸውንና ”መታወቂያ ካርድ ከኤርትራ ሄዳችሁ ውሰዱ” እንደተባሉ እነዚሁ ወጣቶች ተናግረዋል።