(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 16/2010)
ኦሕዴድ የፌደራል የአመራር ስልጣንን የሚፈልገው ሰርቆ ኦሮሚያን ሐብታም ለማድረግ አይደለም ሲሉ አቶ ለማ መገርሳ ተናገሩ።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ዶክተር አብይ አሕመድ የኦሕዴድ ሊቀመንበር መሆናቸውን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የድርጅታቸው አመራሮች በፌደራል ደረጃ ስልጣን የሚይዙት የእኩልነት ስርአት ለማምጣትና ብሔር ብሔረሰቦችን ለማገልገል ነው።
የኦሮሚያው ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ እንዳሉት ከኦሕዴድ ተመርጦ ወደ ፌደራል ስልጣን የሚሄድ ሰው ለኦሮሚያ ክልል የተለየ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲያመጣ አይጠበቅም።
እንደ አቶ ለማ ገለጻ ኦሕዴድ የፌደራል ስልጣንን የሚፈልገው ፍትሃዊና የእኩልነት ስርአት ለማምጣት ነው እናም ኦሕዴድ የፌደራል ስልጣኑን የሚፈልገው ሰርቆ ኦሮሚያን ሃብታም ለማድረግ አይደለም።
አቶ ለማ መገርሳ እንዳሉት ከኦሮሚያ ክልል ለፌደራል የሚመረጠው ሰው ለብሔር ብሔረሰቦች ዋስትና መሆን ይኖርበታል።ይህንን ማሳካትም ለኦሮሚያ ሕዝብ ኩራት ነው ብለዋል።ይህም ሲባል ግን የኦሮሞ ሕዝብን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
በዚሁም መሰረት የኦሮሚያ ክልል አበይት ጉዳዮችን እያከናወነ ነው ሲሉ ተናግረዋል።ስለዚህም በኦሕዴድ ውስጥ የስልጣን ማስተካከያ በማድረግ አዲስ ሽግሽግ እውን ሆኗል ብለዋል።እናም ማን የት ቦታ ቢሰራ ብለን መመዘኛዎችን በማጤን አቅጣጫ ተቀምጦ ዶ/ር አብይ አህመድ የኦሕዴድ ሊቀመንበር ሆነዋል ነው ያሉት።እሳቸውን በተመለከተ ግን እኔ በኦሮሚያ ውስጥ የጀመርኩትን ስራ መጨረስ አለብኝ።ወደፊት አስፈላጊ በሚሆን ጊዜ በፌደራል ደረጃ እድሉን ሳገኝ ሃገሬን አገለግላለሁ ሲሉ ገልጸዋል።ሕዝቡ ለሰጣቸው ፍቅርና አመኔታም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።