ደቡብ ሱዳን ተጠልፈው የተወሰዱ ኢትዮጵያዊያን ህጻናትን እንደምትመልስ አስታወቀች
(ኢሳት ዜና የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ/ም) የደቡብ ሱዳን ፣ የቦማ ግዛት ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ ታፍነው ወደ ደቡብ ሱዳን የተወሰዱ ህጻናትን እንደሚያስመልሱ ቃል ገብተዋል። ሬዲዮ ታማዙጂ እንደዘገበው የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት በቅርቡ ታፍነው ከተወሰዱ ህጻናት መካከል 4 ህጻናትን ማግኘታቸውን ገልጸዋል። እነዚህን ህጻናት ለጋምቤላ ባለስልጣናት እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል።
የአገሪቱ ባለስልጣናትም ሆኑ የጋምቤላ ክልል ባለስልጣናት ሰሞኑን ምን ያክል ኢትዮጵያውያን ህጻናት ተጠልፈው እንደተወሰዱ አላስታወቁም።
የደቡብ ሱዳን የሙርሊ ጎሳ አባላት ወደ ጋምቤላ ክልል በመግባት ህጻናትን እያፈኑ እንደሚወስዱ ይታወቃል። አፈናው አሁንም ድረስ አለማቆሙን የሁለቱ አገር ባለስልጣናት ከደረሱበት ስምምነት ለመረዳት ይቻላል።