በጉራጌ ዞን የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ የደህንነት ተቋማቱን ማስጨነቁን ምንጮች ገለጹ
(ኢሳት ዜና የካቲት 14 ቀን 2010 ዓ/ም) ለ7 ቀናት በወልቂጤና ሌሎችም የጉራጌ ከተሞች የተካሄደው የስራ ማቆም አድማና የአደባባይ ላይ ተቃውሞ ለአገዛዙ የደህንነት አባላት ፈተና ሆኖ መሰንበቱን ምንጮች ገለጹ። ተቃውሞውን ለማስቆም የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የነበሩ የደህንነት አባላት፣ የተጠቀሙባቸው ዘዴዎች ሁሉ ባለመስራታቸውና አድማው አዲስ አበባ ባሉ የጉራጌ ተወላጆች ዘንድም ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ብለው በመስጋት ጭንቀት ውስጥ ገብተው መሰንበታቸውን እነዚህ ምንጮች ገልጸዋል። ወልቂጤ የደህንነትና የጸጥታ መስሪያ ቤቱ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል ሆናለች የሚሉት ምንጮች፣ በተለይ አድማው በአንድ ጊዜ ወደ ዞኑ ወረዳዎች መሸጋገሩ አስድንገጧቸዋል።
የደህንነት መስሪያ ቤቱ በሰጠው አስቸኳይ ትዕዛዝ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ ያሉ የአካባቢው ተወላጅ ባለስልጣናት ከጸጥታ ሃይሉ ጋር ተጣምረው ከህዝቡ ጋር ስብሰባና ውይይት እንዲያደርጉ ታዘው ከህዝቡጋር ንግግር አድርገዋል። ይሁን እንጅ አስተባባሪ ግብረሃይሉ አድማውን የምናቆመውም የምንቀጥለውም በራሳችን ፍላጎትና ውሳኔ መሰረት እንጅ በገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ትዕዛዝ አይደለም በማለት አድማው እስከትናንት ምሽት ድረስ እንዲቀጥል አድርገዋል።
የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት አድማው ዛሬ እንዲጠናቀቅና የንግድ ድርጅቶች እንዲከፈቱ ማድረጋቸውን አስተባባሪ ወጣቶች ተናግረዋል። ተቃውሞአቸውን ጥያቄያቸው እስከሚመለስ ድረስ እነሱ በመረጡትን መንገድ እንደሚያካሂዱ አስተባባሪዎች ገልጸዋል
በዞኑ በተካሄደው ተቃውሞ በርካታ የመንግስት ተሽከርካሪዎችና የባለስልጣናት ቤቶች ወድመዋል።