አራት የወልቃይት የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላትና በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተጠርጥረው የታሰሩ ሁለት ኮሎኔሎች ተፈቱ

አራት የወልቃይት የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላትና በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተጠርጥረው የታሰሩ ሁለት ኮሎኔሎች ተፈቱ
(ኢሳት ዜና የካቲት 14 ቀን 2010 ዓ/ም) ሕገመንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ በማዋቀር፣ የማንነት መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ የታሰሩት አቶ መብራቱ ጌታሁን፣ አቶ አታላይ ዛፌ፣ አቶ ጌታቸው አደመ እና አቶ ተሻገር ወልደሚካኤል ዛሬ ክሳቸው ተቋርጦ ተፈትተዋል። ሰሞኑን በጎንደር እስር ቤት የነበሩት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ መፈታታቸው ይታወሳል።
ይሁንና ሰላማዊ በሆነ መንገድ የአማራ ማንነታችን ይታወቅልን በማለት ጥያቄ በማቅረባቸው የታሰሩት አብዛኞቹ አልተፈቱም። በተለይ ትግራይ ውስጥ በሚገኙ የማሰቃያ እስር ቤቶች በርካታ የወልቃት ጠገዴ ተወላጆች ታስረው አሁንም በስቃይ ላይ ናቸው።
እስካሁን ድረስ ኮሎኔል ደመቀ ገሰሰንና ወ/ት ንግስት ይርጋን ጨምሮ የተወሰኑ የወልቃይት ጠገዴ አስተባባሪዎች ተፈትተዋል።
በሌላ በኩል በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የዕድሜ ልክ ፍርድ ተፈርዶባቸው ከዘጠኝ ዓመት በላይ በእስራት ሲሰቃዩ የቆዩት ኮሎኔል ደምሰው አንተነህና ኮሎኔል ዓለሙ ጌትነት ከቃሊቲ እስር ቤት ወጥተዋል። ሁለቱም የጦር መኮንኖች በእስር ቤት ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል። እንዲሁም የካቲት 14 ቀን 2010 ዓ.ም በእነ ታደሰ መሸሻ የክስ መዝገብ የተከሰሱት አቶ አቻምየለህ ደሴ፣ አቶ አበባው መኮንን፣ አቶ ዓለምአየሁ ደሴ፣ አቶ መልኬ ጌጤ እና አቶ ክንድ ዓለም ክሳቸው እንደተቋረጠ 19ኛ ወንጀል ችሎት አስታውቋል።