እነ ጄኔራል ተፈራ ማሞ አሁንም አልተፈቱም

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 13/2010)

ክሳቸው ተቋርጦ እንዲሁም በፕሬዝዳንቱ ይቅርታ ይፈታሉ ከተባሉ የፖለቲካ እስረኞች ውስጥ እነ ጄኔራል ተፈራ ማሞ እንዲሁም የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበረው ዮናታን ተስፋዬ አሁንም አለመፈታታቸው ታወቀ።

በክስ መቋረጥም ሆነ በይቅርታ ስማቸው ያልተጠቀሰው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌንና የኢትዮጵያ አየር ሃይል አብራሪ መቶ አለቃ በሃይሉ ገብሬን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችም እንዲፈቱ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ መድረክ ዘመቻ ጀምረዋል።

ከጎንደሩ ሕዝባዊ አመጽ ጋር በተያያዘ ከታሰሩት ውስጥ ክሳቸው ተቋርጦ ይፈታሉ ከተባሉት የፖለቲካ እስረኞች ውስጥ በአማራ ክልል የታሰሩት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ጨምሮ የተወሰኑት ሲለቀቁ በፌደራል ወህኒ ቤት የሚገኙት ሌሎቹ እስረኞች አለመፈታታቸው ታውቋል።

የዋልድባ ገዳም እንዳይፈርስ በተለይም ይዞታው እንዳይነካ ሲንቀሳቀሱ የታሰሩት መነኮሳትም ክሳቸው እንደተቋረጠ ቢገለጽም እስካሁን ግን አለመፈታታቸው ታውቋል።

ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞና ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌን ጨምሮ ከሚያዚያ 2009 ጀምሮ ላለፉት 9 አመታት ያህል በወህኒ የቆዩት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በፕሬዝዳንቱ ይቅርታ እንደሚፈቱ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተገለጸው ባለፈው አርብ ነበር።

ይህ ውሳኔ ግን እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ ተግባራዊ አለመሆኑም ታውቋል።

የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበረው ዮናታን ተስፋዬ ይቅርታ እንዲጠይቅ ተጠይቆ እንደሌሎቹ ሁሉ አሻፈረኝ በማለቱ ሌላ የይቅርታ ፎርም እንዳዘጋጁለትም የቅርብ ምንጮች ገልጸዋል።

ይህንንም የይቅርታ ፎርም አልሞላም በማለቱ ዮናታን ተስፋዬ አለመለቀቁም ተመልክቷል።

የግንቦት 7 ዋና ጸሓፊ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከሌሎቹ ተለይተው ወህኒ ቤት የሚቆዩበት ምክንያት የለም በማለት እሳቸውም እንዲፈቱ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ ድረገጾች ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለኢትዮጵያ የተሻለ ነገር በመመኘት፣ምቾታቸውን የሰው የመብት አቀንቃኝ መሆናቸውን በመግለጽም እሳቸውንና ሌሎችን ለማስፈታት ኢትዮጵያውያን እንዲንቀሳቀሱም የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ዘመቻ ተጀምሯል።

በኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ውስጥ በቡድንም ሆነ በግል አቶ አንዳርጋቸውን ጨምሮ የቀሩት የፖለቲካ እስረኞች ሁሉ እንዲፈቱ ግፊቱ መቀጠሉንም መረዳት ተችሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ አየር ሃይል የቀድሞ ማህበር በዋሽንግተን ዲሲ በሃገሪቱ የተለያዩ ወህኒ ቤት የሚገኙ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ባልደረቦች እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል።

የታሳሪ የአየር ሃይል አባላትንም ዝርዝር ባወጣው መግለጫ አካቷል።

እነሱም የመቶ አለቃ በሃይሉ ገብሬ፣የመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ፣የመቶ አለቃ አንተነህ ታደሰ፣የመቶ አለቃ ብሩክ አጥናዬ፣የመቶ አለቃ ዳንኤል ግርማና የመቶ አለቃ ገዛህኝ ድረስ መሆናቸውን የገለጸው የኢትዮጵያ የቀድሞ አየር ሃይል ማህበር በዋሽንግተን ዲሲ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እነዚህ ወጣት መኮንኖች ይፈቱ ዘንድ ግፊት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።