(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 8/2010)
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ከከፍተኛ ማንገራገር በኋላ ስልጣናቸውን ለቀቁ።
በምትካቸውም ሲሪል ራምፖሳ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን ተመርጠዋል።
በሌላም በኩል ታዋቂው የዚምባቡዌ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪና የቀድሞው ፓርቲ መሪና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሞርጋን ቻንግራይ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።
የሙስና ወንጀሎችን ጨምሮ የተለያዩ ክሶች የቀረቡባቸው የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ፓርቲያቸው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ በሳምንቱ መጀመሪያ ስልጣናቸውን እንዲለቁ የሰጣቸውን ማሳሰቢያ እንደማይቀበሉ ትላንት አስታውቀው ነበር።
ምንም ወንጀል እንደሌለባቸው የተናገሩትና ስልጣንም የምለቅበት ምክንያት የለም ያሉት ጃኮብ ዙማ ዛሬ ባልተጠበቀ ሁኔታ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።
የጃኮብ ዙማን ከስልጣን መልቀቅ ተከትሎ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ሊቀመንበር ሲሪል ራምፖሳ በፕሬዝዳንትነት ተመርጠዋል።
በፓርላማው ብቸኛ እጩ ሆነው የቀረቡት እሳቸው እንደነበሩም ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የዚምባብዌ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና ታዋቂው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሞርጋን ቻንጋራይ ትላንት ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።
በደቡብ አፍሪካ በህክምና ላይ የነበሩትና በአንጀት ካንሰር ሲሰቃዩ የቆዩት የ65 አመቱ ሞርጋን ቻንጋራይ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2008 ጀምሮ የዚምባቡዌ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆንም አገልግለዋል።
የቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ብርቱ ተቀናቃኝ የነበሩትና ሁለት ጊዜ ድብደባ፣ሶስት ጊዜ ደግሞ የሀገር ክህደት ክስ የቀረበባቸው ሞርጋን ቻንጋራይ በዚምባቡዌ የሰራተኛ ማህበር መሪ የነበሩና በሮበርት ሙጋቤ በሚመራው ዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ ውስጥ የፖለቲካ ተሳትፎ የጀመሩ መሆናቸውም ታውቋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1999 ሙቭመንት ፎር ዲሞክራቲክ ቼንጅ የሚል ተቃዋሚ ፓርቲ በመመስረትና እጅግ ታዋቂ የሆኑበትን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ባደረባቸውም ህመመ በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ65 አመታቸው በደቡብ አፍሪካ ሕይወታቸው አልፏል።