(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 6/2010)
አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሰባት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ/ኦፌኮ/አመራሮች ከእስር ተለቀቁ።
አመራሮቹ ከእስር እንዲለቀቁ የተደረጉት ክሳቸው ተቋርጦና በይቅርታ መሆኑን ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ገልጿል።
ተከሳሾቹ ችሎት በመድፈር የተፈረደባቸው በመሆኑም ጉዳዩ ወደ ይቅርታ ቦርድ ሄዶ በሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር እንዲወሰን ከተደረገ በኋላ መለቀቃቸውን በሀገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የእነ አቶ በቀለ ገርባ በተፋጠነ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ የተደረጉት በኦሮሚያ የተጀመረው ሕዝባዊ አመጽ እያየለ በመምጣቱ መሆኑንም ታዛቢዎች ይናገራሉ።
ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር ከእስር የተለቀቁት የኦፌኮ አመራሮች ጉርሜሳ አያና፣አዲሱ ቡላላ፣ደጀኔ ጣፋ፣ጌቱ ጋሩማ፣ተስፋዬ ሊበንና በየነ ሩዳ ናቸው።