(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 1/2010)
ሜቴክ ያያ ማዳበሪያ ፋብሪካን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 9 ቢሊየን ብር እንዲከፈለው ጠየቀ።
ማዳባሪያ ፋብሪካው ተሰርቶ መጠናቀቅ የነበረበት ከ6 አመት በፊት እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
በሕወሃት ጄኔራሎች የሚመራው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ከያዛቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል ያያ ማዳበሪያ ፋብሪካ አንዱ ነው።
ሜቴክ ማዳበሪያ ፋብሪካውን አጠናቆ ለመጨረስ የሚፈጅበት ሁለት አመት ብቻ እንደሆነና የፕሮጀክቱ ወጪም 11 ቢሊየን ብር እንደሆነ የገባው ውል ያመላክታል።
ሆኖም የፋብሪካው ግንባታ በውሉ መሰረት በ2 አመት ይጠናቀቃል ቢባልም አሁን ላይ 6 አመት የያዘው የፋብሪካው ፕሮጀክት ከግማሽ በላይ ፈቅ አለማለቱ ታውቋል።
ሜቴክ በ2008 ባወጣው መሪ እቅድ ላይ የተጀመረው የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ባለፈው ስትራቴጂክ ዘመን ስራውን የሚያዘገዩት የፋይናንስና ተዛማጅ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጾ ነበር።
በ2008 መሪ እቅድ ላይ የፕሮጀክት አፈጻጸሙ 34 በመቶ እንደሆነና ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል በሚል ቃል የተገባበት ነበር።
ሆኖም ከሁለት አመት በኋላ በ2010 የፋብሪካው ግንባታ የጠናቀቃል የተባለው ቀርቶ 10 በመቶ ብቻ ጭማሪ በማሳየት ግንባታውን 44 በመቶ ላይ አድርሼያለሁ ሲል ሜቴክ አስታውቋል።
ይህ ብቻ አይደልም ማዳበሪያ ፋብሪካውን አጣናቅቄ ለማስረከብ ተጨማሪ 9 ቢሊየን ብር ያስፈልገኛል ሲል ሜቴክ ለመንግስት ጥያቄውን ማቅረቡ ታውቋል።
ይሄ ደግሞ የአጠቃላይ የፕሮጀክቱን ዋጋ ወደ 20 ብሊየን ብር ከፍ ያደርገዋል ማለት ነው።