(ኢሳት ዲሲ–ጥር 30/2010)
የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት/ኦህዴድ/ 14 የምክር ቤት አባላትን በማባረር እንዲሁም አምባሳደር ብርቱካን አያኖን ጨምሮ 4 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በማገድ ስብሰባውን አጠናቀቀ።
ለአስር ቀናት በአዳማ ያካሄደውን ስብሰባ ትላንት ያጠናቀቀው ኦህዴድ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፣አሳታፊ የፖለቲካ ስርአት እንዲኖርና ሰላምና ፍትህ እንዲሰፍን እንደሚሰራም አስታውቋል።
የኦሮሞ ሕዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን የሀገራችንን ቀጣይ ጉዞ የማቃናት ሚናውን ዛሬም እንደትላንቱ ሊጫወት ይገባልም ብሏል።
የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት/ኦሕዴድ/ “ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝቦች ጋር የነበረንን መልካም ግንኙነት በመመለስ ለዘላቂ ጥቅም በወንድማማችነት መንፈስ እንድንረባረብ የኦሮሞ ባህልና የገዳ ስርአት ባስተማረን መልኩ በታላቅ የሃላፊነት ስሜት በፍቅርና በአብሮነት እንቀሳቀስ” በማለትም ጥሪ አቅርቧል።
በመላ የሀገራችን ሕዝብ ይሁንታ የኦሮምኛ ቋንቋ የፌደራሉ ስርአት የስራ ቋንቋ እንዲሆን እሰራለሁ ብሏል ኦሕዴድ።
በተጨማሪም በሂደት ላይ ያሉና ያልተጠናቀቁ መሰረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች በጥብቅ ዲሲፒሊን እንዲፈጸሙ አቅጣጫ ማስቀመጡንም በመግለጫው አመልክቷል።
በድርጅቱ ውስጥ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ መድረኩ የሚጠይቀውን ትግል በብቃት ለመፈጸምና በቀጣይም ጥንካሬውን አጎልብቶ ለመጓዝ በኢሕአዴግ ምክር ቤት ውስጥ ከነበሩ 45 የኦሕዴድ አባላት አንድ ሶስተኛ ያህሉን ማለትም 14ቱ ተወግደው ሌሎች መተካታቸውን አስታውቋል።
ከድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አራቱን በማገድ ማስጠንቀቂያ መስጠቱንም በመግለጫው አመልክቷል።
የታገዱትም ሆነ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው በስም ባይዘረዘሩም ከቅርብ ምንጮች በተገኘው መረጃ መሰረት የታገዱት በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ወይዘሮ ብርቱካን አያኖ፣አቶ ስለሺ ጌታሁን፣ ወይዘሮ ሰአዳ ከድርና አቶ አብርሃም አድላ ናቸው።
ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው አቶ አህመድ መሀመድ መሆናቸውም ተመልክቷል።
ኦህዴድ በዚህ መግለጫው ለኦሮሞ ሕዝብ፣ለኦሮሚያ ክልል ወጣቶች እንዲሁም ለኦሮሚያ ክልል የጸጥታ አባላትና ለተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ምስጋናውንና ጥሪውን አቅርቧል።
ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጪ ለሚገኙ ተቃዋሚ ሃይሎችም በሙሉ ጥሪ ማቅረቡ ታውቋል።
ድርጅቱ “በአባቶቻችን ተጋድሎ የተገነባችውን ኢትዮጵያን እኛም አስውበንና አንድነቷን አስጠብቀን ለቀጣይ ትውልድ የማሻገር ታሪካዊ ሃላፊነት አለብን” በማለት ጥሪውን አጠናክሯል።
“በዚህ ወሳኝ ወቅት የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት የሚፈተንበት ጊዜ መሆኑ ግልጽ ነው” ብሏል የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በመግለጫው።
“የፖለቲካ ባህላችንን ለማሻሻልና ብሎም የሃገራችንን መጻኢ እድል በጋራ ለማበጀት ተቀራርበን እንስራ”በማለት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተቃዋሚ ሃይሎች ጥሪ አቅርቧል።
ኦህዴድ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ኦዴግ በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው ኦሕዴድ ላቀረበው ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቷል።
ኦዴግ ጥሪው ወቅታዊና ትልቅ ርምጃ ነው በማለት ለጥሪው አዎንታዊ ምላሽ ከመስጠት ባሻገር ከኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ኦሕዴድ አመራሮች ጋር ለመነጋገር ያለውን ፈቃደኝነት ገልጿል።
ኢትዮጵያውያን ለነጻነት፣ለፍትህና ለዲሞክራሲ ለዘመናት የታገሉትና በአስር ሺዎች መስዋዕትነት የከፈሉበት ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ዕውን ሲሆን ለማየት ያለውንም ምኞት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/ገልጿል።